
በተለያዩ ምክንያቶች የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሮች ይደረጋሉ። ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በ አንድ ቀን 1.5 ሚሊየን ዶላር የተሰበሰበበት ዝግጅት በኢትዮጵያ ቀዳሚ በመሆን ብዙዎችን አስገርሟል ።
በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ መስመሮች በ ዩቲዩብ ፤ ፌስ ቡክ ፤ እንዲሁም ቲክቶክ ላይ 12 ሰዐታትን በቆየ የቀጥታ ስርጭት በኢትዮጵያዊያንና በኤርትራዊያን ታሪክ ተሰርቷል።
በኮሜዲያን እሸቱ መለሰ የሚመራው ዶንኪ ቲዩብ በሀገረ አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ብሎም ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ታሪካቸውን ፤ ባህላቸውን ፤ ብሎም ሀይማኖታቸውን እንዳይረሱ በማሰብ ሊመሰረት ለታሰበ ገዳም የገቢ ማሰባሰቢያ ለ 12 ሰዐታት በቆየ የቀጥታ ስርጭት 1.5 ሚሊየን ዶላር ወይም በኢትዮጲያ ዕለታዊ የባንክ ምንዛሬ ከ80 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ችሏል።
ይህም በኢትዮጵያ የ ጎፈንዲ ሚ ወይም የገቢ ማሰባሰቢያ ታሪክ የመጀመሪያውና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገንዘብ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ለመመስረት ላሰበችው ገዳም ከ1497 ሄክታር በላይ ስፋት ያለው መሬት ልትገዛ እንደሆነ ማስታወቋ ይታወሳል።
ለዚህም መሬት ግዢ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መክፈል ይጠበቅባታል። ታዲያ በዶንኪ ቲዩብ እንዲሁም በተለያዩ የመድረክ ስራዎች የሚታወቀው ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ ለዚህ ቦታ መግዣ በዶንኪ ቲዩብ ስም አንድ ሚሊየን ዶላር ሳናሰባሰብ አንወጣም በማለት ከቀኑ 8 ሰዐት ከ አርቲስት መሰረት መብራቴ ጋር በመሆን በ ዩቲዩብ ፤ ፌስቡክ እንዲሁም ፤ በቲክቶክ ገቢ ማሰባሰቡ በቀጥታ ስርጭት ተጀመረ።
በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ሚሊየን ዶላር በአንድ ቀን ተሰብስቦ አይታወቅምና ብዙዎች ቢያንስ ግማሹ ከተገኘ ጥሩ በማለት ድጋፋቸውን ቀጠሉ።
የገቢ ማሰባሰቢያው ከተገኘው የገንዘብ መጠን በላይ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ጎልቶ የታየበት ነበር ። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የሌላ እምነት ተከታዮች ለዚህ ቤተክርስቲያን ማሰሪያ ያላቸውን ሲረዱ የተመለከትንበትም ጭምር ።
ከቀኑ ስምንት ሰዐት የተጀመረው የቀጥታ ስርጭት እንደቀጠለ ነው ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌን ጨምሮ ሌሎች የጥበብ ሰወች ተቀላቅለዋል ከመላው አለም ይደወላል ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰወች ዝግጅቱን እየታደሙ ነው። ቀጥታ ስርጭቱ ያለምንም እረፍት 12 ሰዐታትን አስቆጠረ። በመጨረሻም አንድ ሚሊየን ዶላር ለመሰብሰብ የታቀደበት ፕሮግራም 1.5 ሚሊየን ዶላር በመስብሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ሆነ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-11-14