ሀገሬ ቲቪ

የተፈናቃይ ዜጎችን ችግር ያቃለለው ፕሮጀክት

በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የሚሳተፈው ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ግብረሰናይ ድርጅት በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የማኀበረሰቡን ችግር የሚያቃልሉ የተለያዩ ፕሮጅርክቶችን እየሠራ ይገኛል።

በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በደብረብርሀን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎችም የንጹህ መጠጥ ውኃ እንዲያገኙ አድርጓል በተጨማሪ ለነዚሁ ተፈናቃይ ዜጎች የመጸዳጃ እና የመታጠቢያ አገልግሎት የሚሰጡ ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።

እነዚህ መሠረተ ልማቶች የነበረብንን ተደራራቢ ችግር አቅልሎልናል ሲሉ ያናገርናቸው ተፈናቃይ ዜጎች ተናግረዋል።

ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በሰሜን ሸዋ እንዲሁም በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች እየሰራ ላለው የንጽሁ ወኃ አቅርቦት እና የንጽህና መስጫ ተቋማት ፕሮጀክት ከዩኒሴፍ ባገኘው 70 ሚሊዮን ብር እንደኾነ የወሽ ፕሮጀክት ማናጀር የኾኑት አቶ ወንደሰን አድማሱ ነግረውናል።

በፊት ላይ አንድ መጸዳጃ ቤት ብቻ በመኖሩ ከፍተኛ መጨናነቅ እንደነበር አስታውሰው አሁን በ አራት ብሎክ እያንዳንዳቸው አምስት ክፍል ያሉዋቸው መጸዳጃ ቤት ተሰርተዋል ብለውናል።

እነዚህ የተገነቡት የመጸዳጃ እና የመታጠቢያ ቤቶች ከ 13 ሺ በላይ ተፈናቃይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ይሁን እንጂ ከተጠቃሚው ቁጥር አንጽር የሚያንስ እንደኾነ አቶ ወንድወሰን ይስማማሉ።

አሁንም ቢኾን የንጽህና አገልግሎት መስጫ ቤቶቹን ለማስፋት ዝግጁ እንደኾኑ ገለጸው፤ የቦታ ጥበት ግን ግንባታዎቹን ለማስፋት ተግዳሮት ኾኖብናል ብለዋል።

ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከደብረብርሀን በተጨማሪ በአጣዬ በሸዋሮቢት እና ሌሎች አካባቢዎች ንጹህ የመጠት ውኃ በመገንባት ለሕብረተሰቡ አስረክቧል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-11-15