ሀገሬ ቲቪ

“የሀገራችን ኢኮኖሚ የገጠሙትን ጫናዎች ተቋቁሞ መቀጠል ችሏል።” ጠ/ሚ አብይ አህመድ

የሀገራችን ኢኮኖሚ ዓለም አቀፋዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች ተረባርበው ቢፈትኑትም የገጠሙትን ዕክሎች ተቋቁሞ መቀጠል መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ይህንን ያሉት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምላሽ በሰጡበት ሲሆን ኢኮኖሚያችን በዚህ ዓመት የ7.5 በመቶ ዕድገት እንዲኖረው እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል። በ2014 በጀት ዓመት የጂዲፒ ዕድገታችን 6.4 በመቶ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባሳለፍነው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የፋይናንስ ዘርፉ በሰሩት ስራ የአገልግሎት (ሰርቪስ) ዘርፉ የ7.9 በመቶ የተሻለ ዕድገት አስመዝግቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የግብርናው ዘርፍም የ6.1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የስንዴ ምርት ማሳደግ ላይ ከተሰራው ስራ በተጨማሪ ሩዝን ከውጭ ማስገባትን ማቆም የሚያስችል አቅም መታየቱን ጠቁመዋል።

የውጭ ምንዛሬ ዕድልን ለሀገር ውስጥ ምርቶች ሲባልም በጣም አስፈላጊ ያልሆኑ ምርቶች ላይ የተጣለው ዕገዳ ይቀጥላል ምብለዋል።

ከሕወኃት ጋር ስለተደረሰው ስምምነትም ለሰላም እና ዕድገታችን ስንል ሰላምን መርጠናል ብለዋል።

የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ የደቡብ አፍሪካው ስምምነት ወልቃይት ወዴት ይካለል የሚለውን የሚወስን ሳይሆን ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ያስቀመጠ ሲሆን የአካባቢው ጉዳይ በህግ አግባብ እና በውይይት እንዲፈታ እንሰራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከኦነግ ሸኔ ጋር በተያያዘ ሰላም ማስጠበቁ ላይ መንግስት ጠንክሮ እየሰራ ለሰላም እና ውይይት ግን ሁሌም ዝግጁ ነን ብለዋል።

ፓርላማው ፕሬዘዳንት ሳህለውርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክርቤቶች ላይ ያቀረቡትን ንግግር የተመለከተውን የድጋፍ ሞሽን በአንድ ተቃውሞ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-11-15