ሀገሬ ቲቪ

የዲጂታል ዘርፉን ደህንነት መጠበቅ

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ዘርፉን ደህንነት ለመጠበቅ እና የህዝቡን የዲጂታል ዕውቀት ማሳደግ ላይ እየሰራሁ ነው አለ። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ናት ።

የዲጂታል ዘርፉ በሀገራችን እያደገ የመጣ ዘርፍ ነው። እንደሀገር የተለያዩ የዲጂታል ስርዓቶችን እየገነባን ነው ያሉን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ሁሪያ አሊ የዘርፉ ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆንም እየሰራን ነው ብለውናል።

አዳዲስ የዲጂታል ስርዓት እየገነባን እና አሰራሮችን ወደ ዲጂታል እያመጣን ባለንበት በዚህ ጊዜ የዘርፉ የሳይበር ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል።

ወደ ዲጂታል ዓለም እየተቀላቀልን ባለንበት የዲጂታል ተጠቃሚው ማህበረሰብ በዘርፉ ላይ ያለው ዕውቀት እንዲያድግ ይበልጥ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመውናል።

የዲጂታል ዘርፉ ላይ እየሰራን ባለነው ስራም 17ተኛውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ሃገራችን እንድታዘጋጅ መመረጧ ብዙ ልምዶችን ከተሳታፊዎች እንድንቀስም ያደርገናል ብለዋል።

ኢንተርኔትን የሚመለከቱ ሀሳቦች በሰፊው የሚነሱበት እና ከ2500 በላይ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ተሳታፊዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀው ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አስተዳደር ጉባኤ ከህዳር 19 እስከ 23 በሀገራችን ይከናወናል።

በአብርሃም በለጠ
2022-11-17