
አፍሪካ የተፈጥሮ ሃብቴን አውጥቼ ኃይል ላምርት ማለቷ በግብጹ የኮፕ 27 ጉባኤ የክርክር ምንጭ መሆኑ ተገለጸ።
የአፍሪካ መሪዎች የተፈጥሮ ጋዝን አምርተን ኢኮኖሚያችን እንደግፍ ቢሉም የዓየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የያዝነው ዕቅድ ያዛባብናል የሚል ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
አፍሪካ እንደአህጉር የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ ተጠቅማ የመልማት ዕድሏን አልተጠቀመችም የሚሉ ሃሳቦች ሲንጸባረቁ ቆይተዋል። ዛሬ ዛሬ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።
ይሁንና ግን የሃይል አማራጭ መሆን የሚችሉ ሀብቶቿን አውጥታ የመጠቀም ውጥኗ ላይ ተቃውሞ ገጥሟታል፤ ምነው የዓለም ሙቀት እየገረፈን አፍሪካ ስለምን ተጨማሪ በካይ የሆነውን የተፈጥሮ ነዳጅ ካላወጣሁ አለች የሚል።
ከአፍሪካ በኩል ደግሞ በኢኮኖሚው የመበልጸግ ፍላጎቴስ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ይሄው ጉዳይ በተካሄደው የዓየር ንብረት ጉባኤ ኮፕ 27 ላይ የክርክር ምንጭ ሆኗል።
የአፍሪካ ሀገራት ቅድሚያ ድህነትን ለማጥፋት የተፈጥሮ ሃብታችንን አውጥተን ህዝባችንንም ኢኮኖሚያችንንም እንደግፍ የሚል አቋምን ይዘው በጉባኤው ላይ ጥያቄን አቅርበዋል።
አፍሪካ የተፈጥሮ ጋዟን ብታወጣ እና ኢኮኖሚዋን ብትደግፍ የጋዝ የብክለት አቅምም ከድንጋይ ከሰል እና የነዳጅ ዘይት ያነሰ ነው የሚል መከራከሪያንም አቅርበዋል።
በርግጥ የተፈጥሮ ጋዝ ከከሰል እና የነዳጅ ዘይት ያነሰ የብክለት አቅም እንዳለው በአውሮፓ ህብረትም ቀደም ብሎ ቅቡልነት ያገኘ ሃሳብ ነው።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪዉሚ አዴሲና አፍሪካ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብት አላት ይህም በኮፕ 27 ጉባኤ ላይ ሊንጸባረቅ ይገባል ብለዋል።
“አፍሪካ ሁሉንም የተፈጥሮ ጋዝ ሃብቷን ለኃይል ብትጠቀም እንኳን የሚኖራት የብክለት መጠን አሁንም ዝቅተኛ ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ አፍሪካ ከታዳሽ ኃይሏ በተጨማሪ የተፈጥሮ ጋዝ ሃብቷን የሃይል አቅርቦቷን እና ደህንነቷን ለማረጋገጥ ልትጠቀም ይገባል።”
የአፍሪካ ሀገራት ይሄንንው ሃብታችንን አውጥተን መጠቀማችን በሩስያ ዩክሬይን ጦርነት የሃይል ቀውስ ውስጥ ለገባው የአውሮፓ አህጉርም ቢሆን አማራጭ እንሆነዋለን ብለዋል። ለዚህም የገንዘብ ድጋፍን ጠይቀዋል። ይሁንና ግን የዓየር ብክለትን ለመቀነስ የምናደርገውን ትግል ያዛባብናል የሚል ምላሽን ከለሎች ሀገራት ተንጸባርቋል።
ህንድን ጨምሮ የተወሰኑ ሃገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ወደ ታዳሽ ኃይሎች የምናደርገውን ጉዞ ለማፋጠን የተፈጥሮ ጋዝን ጨምሮ የትኛውንም አዳዲስ የነዳጅ ፕሮጀክትን መደገፍ አይገባም ባይ ናቸው።
አፍሪካ ግን እናንተ በበከላችሁት አየር የመጣው ጉዳት የደቆሰው እኔን ነው ደግፉኝ ስል ከቃል ባለፈ የተግባር ድጋፍ አላሳያችሁኝም ስለዚህ አሁን በተፈጥሮ ጋዝ ልማት ህዝቦቼን ከድህነት ላውጣ ስል ብክለት እንደመክራካርያ ማንሳት ተግቢ አይደለም በሚለው ሀሳቧ ጸንታለች ።
የአፍሪካ መሪዎች ከበካዩ የነዳጅ ኃይል የአውሮፓ በትልቁ ተጠቅሞ ሲያበቃ እኛ እንልማ ስንል ሊያቆመን አይገባም ብለዋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-17