ነገሩ ስልጣን መቼ ይጠገባል አይነት ነው። 43 ዓመታትን የመሯትን ሀገራቸውን ዳግም ለመምራት ምረጡኝ የማለታቸው ነገር ወይ አፍሪካም አሰኝቷል።
ሰውየው ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉሜ ምባሶጎ ናቸው። ዕድሜያቸው 80 ደርሷል። ከእድሜያቸው ከግማሽ በጥቂቱ እልፍ ያለውን ያሳለፉት ከ1961 ዓ.ም. በኋላ ነፃነቷን ያገኘችውን ሀገር ኢኳቶሪያን ጊኒን በመምራት ነው።
የሀገራቸው ነፃነት ሊስተካከል የሚችል ዘመንን በስልጣን ላይ ነበሩ፤ አሁንም በወንበራቸው ላይ መደላደልን መርጠዋል።
እሳቸው በሚመሩት ሀገር ላይ የምርጫ እጩ መሆን እንጂ ማሸነፍ የቅዠት ያህል ነው ይባልላቸዋል።
ሀገሪቱን በፕሬዚዳንትነት በመሩባቸው 4 አስርት ዓመታት ለሀገሬ ሰው የሚታይ ለውጥን ማምጣት አልቻሉም እየተባሉም ይተቻሉ።
በሀገሪቷ ካዝና ከዜጎቻቸው ይልቅ ዘመድ አዝማዶቻቸውን እና ልጆቻቸውን አንደላቀውበታል። በተፈጥሮ ጋዝ በታደለችው ሀገር እሳቸው ፈላጭ ቆራጭ ናቸው።
የሀገሪቱ የነፃነት አቀንቃኞች እና የፖለቲካ ምሁራን ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ የሚሳተፉበት የሚቀጥለው ምርጫ እንደው ለይስሙላ ነው ባይ ናቸው።
እንደው ምን አለፋቹ ሰውየው ለቀጣይ ዘመን ሀገሪቱን ለመምራት 95 በመቶ በሆነ ድምይፅ መመረጣቸው አይቀርም ሲሉም ይናገራሉ።
በዚያች ሀገር የልብን አውጥቶ መናገር ቅንጦት ነው፤ በሰብዓዊ መብት ረገጣም ቢሆን ስሟ ደጋግሞ ይነሳል። ፕሬዝዳንቱ ሰዎችን በማሰቃየት እና በመሰወር ይከሰሳሉ።
በዚህ ሁሉ ውንጀላውስጥም ቢሆን ፕሬዝዳንቱ ሀገሬ ምርጫ ታደርጋለች እኔም ለቀጣይ የምርጫ ዘመን እወዳደራለው ብለዋል።
ከስፔን ነፃ ከወጣች 54 ዓመታትን የተሻገረችውን ሀግር ኢኳቶሪያል ጊኒን ለ43 ዓመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉሜ ምባሶጎ ወንበራቸውን ተቀምጠውበት ይዘልቁ ይሆን፤ ግዜ ሁሉንም ይመልስልናል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-11-21
