የጤና ተቋማት በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ሪፖርት አለማድረጋቸው ችግሩን ለመቅረፍ ፈተና ሆኗል ተባለ።
የመረጃው በትክክል መቅረብም ከእናቶች እና ህጻናት ሞት ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች እና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ከ 2000 ዓ.ም ጀመሮ ባደረገችው ርብርብ ከግማሽ በላይ የቀነሰች ቢሆንም አሁንም ግን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው እናቶች በወሊድ ምክንያት እደሚሞቱ ጥናቶች ይጠቁማሉ ።
ጤና ሚኒስቴር የ እናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ ይረዳል በማለት ከጤና ተቋማት በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ሪፖርት መሰብሰብ ከጀመረ 8 ዓመታትን አስቆጥሯል ።
ታዲያ ይህ መንገድ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ያለው አስተዋጾ ከፍትኛ ቢሆንም የጤና ተቋማት መረጃዎችን በወቅቱ አለመስጠት የተያዘውን እቅድ ለመፈጸም ፈተና እንደሆነ በጤና ሚኒስተር የእናቶችና የህጻናት ጤና እና ስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም ተናግረዋል ።
በ እርግዝና ወራት ተገቢውን ክትትል አለማድረግ እንዲሁም ምጥ በመጣ ጊዜ በቤት ውስጥ ለመውለድ የሚደረገው ጥረት ለ እናቶች ሞት ቀዳሚ መንስኤ እንደሆነ ይታወቃል ።
በአንዳንድ የክልል ከተሞች እናቶች በጤና ተቋማት ለመውለድ ቢፈልጉም መንገዶችን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች አስቸጋሪ መሆን ግን ካሉበት እንዳይንቀሳቀሱ ሲያግዳቸው ይስተዋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የኢ/ያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ አሳስበዋል።
ለእናት ሞት መንስኤ የሆኑትን ችግሮች በውል በመረዳት በታሰበው ልክ መቀነስ ይቻል ዘንድ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጾ እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-11-21
