ሀገሬ ቲቪ

ለኮንጎው ፕሬዝዳንት መጪው ምርጫ ፈታኝ እንደሚሆንባቸው ተገለጸ

ለመጀመሪያ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ወደስልጣን የመጡት እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ለአራት አመታት እያስተዳደሩ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺስኬዴ መጪው የ2023 ምርጫ አስቸጋሪ እና ፈታኝ የሆንባቸዋል ተባለ።

ፕሬዝዳንቱ በአማጺያን የምትታመሰዉን ሀገሪቱን ሰላም ለማድረግ የሰሩት ስራ ቀድመዋቸው ከነበሩት ፕሬዝዳንት ጋር ሊነጻጸርም እንደሚገባ ተገልጿል።

በስልጣን ሽኩቻ እና ስልጣንን በሃይል አልያም በመፈንቅለ መንግስት የሚይዙ መንግስታት መለያዋ እየሆኑ የመጣችው አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደስልጣን በመምጣት ሰላማዊ መሪ የሆኑት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ሼሴኬዲ በ2023 የሃገሪቱ ምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ተሰምቷል።

ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼሴኬዲ በሰላማዊ ሽግግር ወደ ስልጣን የመጡ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት በመሆን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን እብሪተኝነት ሰብረው በ2019 ስልጣን ለመያዝ በቅተዋል።

ይሁን እንጂ ለአራት አስርት አመታት በውስጣዊ እና በወጫዊ ሃይሎች ስትናጥ የቆየችውን ሃገር እንዳሰቡት ወደ ስላም እና መረጋጋት አምጥቶ መምራት ቀላል አልሆነላቸውም። በተለይም ደግሞ በሃገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የሚንቀሳቀሰው እና M23 የተሰኘው አማፂ ቡድን ለሃገሪቱ ሰላም ማጣት እና ለፕሬዝዳንቱ እጅግ በጣም ፈተና ሆኖባቸዋል።

በዚህም ምክንያት የሃገሪቱ የመከላከያ ሃይል አማፂ ቡድኑን ለማጥፋት በሚያደርገው ውጊያዎች ሳቢያ ንፁሃን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በዚህም መንግስታቸው ሲነቀፍበት ቆይቷል።

የኮንጎ ፓርላማ ባወጣው መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2012 ድረስ እልቂቱ አነስተኛ ቢሆንም እ.ኤ.አ. በ2019 እስከ 2021 ድረስ ግን በአማፂያኑ ምክንያት የሚፈናቀሉት እና ህይወታቸውን የሚያጡት ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን መረጃው ያሳያል።

በ2019 በነበረው የሃገሪቱ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ አሸንፈው ወደ ስልጣን ሲመጡ ሃገራቸውን የተረጋጋች እና ሰላማዊ ለማድረግ ቃል የገቡ ቢሆንም በሃገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ኤም 23 አማፂ ቡድንን የሚያደርሰውን ጉዳት አሁንም ማስቆም አልቻሉም። ይሄው ሁነትም በፕሬዝዳንቱ የቀጣዩ የሀገሪቱ ምርጫ ተሳትፎ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው እየተጠቆመ ነው።

ፌሊክስ ሺስኬዲ ከሳቸው በፊት የነበሩት የኮንጎ ፕሬዝዳንት ዮሴፍ ካቢላ ሰላም የማምጣት ስራ ጋር ምን እንደሰሩ መነፃፀር እንዳለባቸው ፖለቶከኞች ያስረዳሉ።

ይሄው ሰላምን በሀገሪቱ ለማምጣት ከሚሰራው ስራ አንጻር ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ለአራት አመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺስኬዲ መጪው ምርጫ ከባድ እና ፈታኝ እንደሚሆንባቸው ከወዲሁ እየተገለፀ እንደሚገኝ ኢስት አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል።

በማህሌት አማረ
2022-11-21