በህንድ ሃገር የምትኖር አንዲት ሴት በቅዶ ህክምና ባለሙያ ሁሉቱም ኩላሊቶቿ ተሰርቀዋል።
ነገሩ ምን መሰላችሁ ሱኔታ ዴቪ የተባለችው የ38 አመት ግለሰብ ባደረባት የጤና እክል ምክኒያት ማህፀኗ እንደሚዎጣ በህክምና ባለሙያዎች ይነገራታል።
ሲኒታም ፈጣሪ ያመጣውን ማን ይመልሰዋል ማህፀኔ ወጥቶ ጤነኛ የምሆን ከሆን ይሁን ብላ ከህክምና ባለሙያዎች ቀዶ ጥገናው የሚደረግበት ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷት ወደ ቤቷ ትመለሳለች፡፡
ይህች የ38 አመት ሴት በተሰጣት ቀነ ቀጠሮ መሰረት ከምትኖርበት አካባቢ ሙዛፈርፑር ወደ ባርያርፑር በሚገኘው የግል ክሊኒክ ሱብ ካሃንት አመራች፡፡
ነገር ግን እንደጠበቀችው ማህፀኗ ወጥቶ ጤነኛ መሆን ሳይሆን የገጠማት እጅጉን ልብ የሚሰብር እና ተስፋ የሚያሳጣ ነበር። ምክኒያቱም በቀዶ ህክምናው ጊዜ ማህፀኗ ሳይሆን የወጣላት ሁለቱንም ኩላሊቷን በሃሰተኛ የህክምና ባለሙያ ተሰርቆ መወሰዱን ማወቋ ነበር።
ከወራቶች በፊት እንደዚሁ በህንድ ሃገር የምትኖር አንዲት ሴት ባለቤቴ ከህክምና ዶክተሮች ጋር በመመሳጠር አንዱን ኩላሊቴን ሰርቆ በጥቁር ገበያ ሸጦብኛል ስትል ከሳ እንደነበር የቀርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ታዲያ ይሄው ተግባር በሱኒታ ዴቪ ጋርም ለሁለተኛ ጊዜ ተደግሟል።
ሀኪሞች ኩላሊቷ እንደተሰረቀ እና አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ካላደረገች እንደምትሞት ሲነግሯት በጣም መደንገጧን የገለጸችው ህንዳዊት ሴት ሱኒታ በሲሪ ክርሽና ሜዲካል ኮሌጅ እና ሆስፒታል መደበኛ የኩላሊ እጥበት እያደረገች ትገኛለች፡፡
በሲሪ ክርሽን ሜዲካል ኮሌጅ እና ሆስፒታል የሚገኙ ዶክተሮች ከቀዶ ጥገናው በኋላ ወደ ሆስፒታላቸው የመጣችው የሱኔታ የጤና አሁኔታ አሳሳቢ ሲሆንባቸው ባደረጉላት የህክምና ክትትል ሁለቱም ኩላሊቶቿ መሰረቁን እንዳወቁ ነበር ለቤተሰቦቿ ለአንድ ቀን እንኳን ዲያሊስስ ሳታደርግ ከቆየች ወዲያውኑ ህይወቷ ሊያልፍ እንደሚችል የተናገሩት፡፡
የሱኔታ ቤተሰቦችም ሁኔታውን እንዳወቁ የሱብ ካሃንት ክሊኒክ ባለቤት ላይ እና የክሊኒኩ ሰራተኛ በሆነው በዶ/ር አር ኬ ሲንግ ላይ ክስ መሰረቱ።
ፓሊስም የደረሰውን ጥቆማ ይዞ ባደረገው ማጣራት ክሊኒኩም ሆነ ዶክተሩ ፍቃድ የሌላቸው እና በሃሰተኛ መረጃ የሚሰሩ መሆኑን ይደርስበታል። የክሊኒኩን ባለቤት እና ሃሰተኛ ዶክተር ተብየውንም በማደን ላይ ነው።
ሱኔታ በህይወት ለመቆየት በየቀኑ ከምታደርገው ዲያሊስስ በተጨማሪ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ካላደረገች የመኖር እድሏ ጠባብ መሆኑን የህክምና ክትትል የሚያደርጉላት ዶክተሮች ቢናገሩም ቅሉ ግን ንቅለ ተከላውን ለማድረግ ብዙ ወረፋዎችን መጠበቅ ግድ ብሏታል።
በማህሌት አማረ
2022-11-22
