በሀገራችን ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኘ አለመሆኑ ተገለጸ። በአስር ዓመት ውስጥ ሁሉንም ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ውጥን ተይዞ እየተሰራ ቢሆንም አሁንም ቢሆን አፈጻጸሙ እንደሚጠበቀው አለመሆኑ ተጠቁሟል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ባንክ በተገኘ የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር በአስር ዓመት ውስጥ ሁሉንም ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ብሄራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተይዞ መስራት ከጀመረች አራት ዓመታትን አስቆጥራለች።
የዚሁ ፕሮግራም አፈጻጸም ላይ ውይይትን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አካሂዷል። አሁንም ቢሆን ግን በሀገራችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኘ ያለው ህዝብ 48.3 በመቶ ያክሉ ብቻ መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ የግሉ ዘርፍ በዘርፉ ላይ ያለው ተሳትፎ አነስተኛ መሆንን ጨምሮ የፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የሰው ሀብት ጋር የተያያዙ ችግሮች ዕቅዱ እንደሚፈለገው ተፈጻሚ እንዳይሆን አድርገውታል ብለዋል።
የብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ውስንነትን ለመቅረፍ እየሰራ ነው ያሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላ ሀገራችን የቆየችበት ጦርነትም የታየዘው ዕቅድ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸውልናል።
የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሙ በ1998 ዓ.ም. ሲጀመር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ የሆኑት 690 ያክል ከተሞች የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ 8 ሺህ ከተሞች ተደራሽ መሆናቸው ተነስቷል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ መሆን ያልቻሉ የገጠር የሃይስኩል ት/ቤቶች እና ቀበሌዎች ከጸሐይ ኃይል ጭምር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን የኢነርጂ ዘርፍ አማካሪው አቶ ጎሳዬ መንግስቴ ተናግረዋል።
እስከ 2022 ዓ.ም. በሚቆየው ዕቅዱ 65 በመቶ የሚሆነውን የሀገራችንን ህዝብ ከዋና የኤሌክትሪክ መስመር ቀሪውን 35 በመቶ ከሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ የማድረግ ውጥን ተይዟል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-22
