ሀገሬ ቲቪ

ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሰራ ቤት

ቤት ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው። ደሰስ ካሉ ጎጆዎች እስከ ቅንጡ ቪላዎች አለማችን በውስጧ አቅፋለች። ከሰሞኑ ታዲያ ቤት ብቻ ሳይሆን ሙዚየምም መሆን የሚችል ቤትን መስራት ፈልገው ስላደረጉት ሰው ሰማንና ልናጋራቹ ወደደን ።

ቫን ትሩንግ ይባላሉ ቬትናም አሉኝ ከምታለቸው ባለጸጋዎች አንዱ ናቸው ። ከሰወች ለየት ብሎ መኖር የሚያስደስታቸው እኚ ሰው በአንድ ወቅት አንድ ቅንጡ ቤት መስራት ይፈልጋሉ ።

ሀሳባቸው አስገራሚ መኖሪያ ቤት መስራት ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ የቱሪስት መስህብ እየተጎበኘ ለሀገራቸው ተጨማሪ ገቢ የሚያስገባ ታሪካዊ ቤት መስራት ነበር። ባለሀብቱ የሚሰሩትን የቤት አይነት ከመውሰናቸው በፊት ዐለም ላይ ያልተለመዱ ቅንጡ ቤቶች አሉባቸው ብለው ያሰቧቸውን ከተማዎች መጎብኘት የመጀመሪያ ስራቸው አደረጉ ።

ከጉብኝታቸው በኋላም ዓለም ላይ እምብዛም ያልተመለከቱትን የቤት አይነት ሊሰሩ ወሰኑ ። ከውጪ በሩ ጀምሮ ጠቅላላ የውስጠኛው ክፍል በወርቅ የተለበጠ ቤት እንዲሰራ ለባለሞያዎች አማከሩ ።

ያነጋገሯቸው መሀንዲሶች ይህ አይነቱ ቤት በሀገሪቱ አልተለመደምና እንዴት ሊሆን ይችላል ብለው ቢከራከሩም ባለሀብቱ ግን የለም ከ ሀሳቤ ንቅንቅ አልልም አሉ።

በመጨረሻም ብዙዎች አምነው መቀበል የተሳናቸው ቤት በሶስት ዓመት ውስጥ ተሰርቶ ተጠናቀቀ ። የመግቢያው በር ፤ ግድግዳው ፤ የመብራት ማንጠልጠያዎች ፤ መቀመጫዎች ፤ የኩሽና ዕቃዎች ፤ መጸዳጃ ቤት ፤ ማብሰያ ድስቶች ምን አለፋቹ በጠቅላላ በወርቅ የተለበጡ ናቸው ።

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ቅርጾች በወርቅ ያሸበረቁ ሀውልቶች እና ሌሎች ጋጣጌጦች የቤቱ ድምቀት ናቸው ። ባለሀብቶ ይህን ቤት ለመስራት ሲነሳ ለመኖሪያነት አስቦት የነበረ ቢሆንም ከሀገሬው ሰው ውጪ ከተለያዩ የዐለማችን ክፍሎች ጎብኚዎች ይሄን ቤት ለማየት ወደ ቬትናም በመትመማቸው ሙሉ በመሉ ለቱሪስቶች ክፍት እንዲሆን አድርገውታል ።

በርካቶች ይህን ቤት ካዩ በኋላ አምነን መቀበል ከብዶናል ምክንያቱም አንድን ቤት ከመግቢያው ጀመሮ በወርቅ መለበጥ ከባድ ነውና ይላሉ ።

ባለሀብቱ ለዚህ ስራ ስንት አወጡ ቢባሉም እሱ ይቆየኝ ማለትን መርጠዋል ። ነገር ግን በህይወቴ ከሰራዋቸው ስራዎች ሁሉ የምኮራበት ስራ ነው ገና ሌሎች ነገሮችን ጨምሬ ማስደመሜን እቀጥላልሁ ሲሊ ተደምጠዋል ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-11-23