ሳይንስ የሰውን ልጅ አመጣጥ ለማጥናት የጥንት ቅሪተ አካላትን ማጥናትን እንደመንገድ ይዟል። በቅሪተ አካላት ጥናት ደግሞ አፍሪካ በተለይም ምስራቅ አፍሪካ የጥንታዊ የሰው ልጅ መገኛ እንደሆነ ይታሰባል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የዚህ የአፍሪካ ክፍል አካል እንደመሆኗ በሰው ልጅ ጥንታዊ ቅሪተ አካላት ጥናት ውስጥ ስሟ በትልቁ ይነሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጥንታዊ የሰው ቅሪተ አካላት አንዷ ሉሲ የተገኘችው በዛሬዋ ዕለት በ1987 ዓ.ም. ነበር።የሉሲ ቅሪተ አካል በሰሜን ምስራቃዊ የሀገራችን ክፍል በአፋር መገኘት ለጊዜው የቅሪተ አካል ጥናት ትልቅ ግኝት ነበር።
ይሄው ግኝት በጥንታዊ የሰው ልጅ ቅሪተ አካል ምርመራ የሰው ልጅ በሁለት እግሩ ቆሞ መሄድ የቻለው ከ ሶስት ሚሊዮን አመታት በፊት ነው የሚል ፍንጭን ሰጥቷል።
ይሄው የአርኪዮሎጂ ጥናት ግኝት የተከናወነው ደግሞ የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር በሆኑት አሜሪካዊው ዶናልድ ጆንሰን እና የጥናቱ ረዳታቸው ቶም ግሬይ ነበር። በአፋር ሃዳር ቡድኑ ባደረገው የቅሪተ አካላት ጥናት ሉሲ ተገኝታለች።
በርግጥ የጥናቱ መሪ ዶናልድ ጆንሰን የጥንታዊ የሰው ዘር ቅሪት በስፍራው ሊገኝ እንደሚችል ግምቱ ነበራቸው። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ በሀዳር ቀደም ብሎም የጉልበት መገጣጠሚያ አጥንት ተገኝቶ ነበር።
ቡድኑ በስፍራው ላይ ያለውን ተስፋ ይዞ ባደረገው ፍለጋ የጥንታዊ ቅሪት የእጅ አጥንትን አስቀድመው ማግኘት ችለዋል። በሁለት ሳምንት ውስጥም በመቶዎች የሚቆጠሩ ቁርጥራጭ ቅሪቶችን ማግኘት ችለዋል።
የተገኘው ቅሪት ሲጋጠምም 40 በመቶ የሚሆን የጥንታዊ የሰው ዘርን ሙሉ ቅሪት የሚሸፍን ሆኗል። ይሄው ቅሪትም ከ3.2 ሚሊዮን ዓመት በፊት የኖረች ጥንታዊ የሰው ዘር ቅሪት መሆኑን አጥኝዎቹ አረጋገጡ።
የፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰን የቅሪት ፈላጊው ቡድን የዚህችን ጥንታዊ አጽም ካገኘ በኋላ በዚያችው ምሽት ደስታውን የቢትልስ ሙዚቃ የሆነውን ‘’ሉሲ ኢን ዘ ስካይ ዊዝ ዳይመንድስ’’ የተሰኘውን ስራ ደጋግመው በማድመጥ አክብረውታል።
በዚህም ሳቢያ ስሟ ሉሲ እንዲባል አድርገዋል። በርግጥ በሀገረኛ ስሟ ድንቅነሽ ተብላ ትጠራለች።በአፋር ሀዳር ሉሲ ከተገኘች በኋላ ባሉት ዓመታት ከጥንታዊ የሰው ዘር ቅሪተ አካላት 13 ያክል ተገኝተዋል።
ሉሲ ቀድሞ ያልታወቀ የጥንታዊ የሰው ዘር አካል የሆነው የአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ዝርያ ስትሆን ኢትዮጵያ በሴኩላር ሳይንስ የቅሪት አካላት የሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ እንድትባልም ምክንያት ሆናለች።
በሉሲ ግኝታቸው ዓለም አቀፋዊ ሽልማትን ማግኘት የቻሉት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰንም የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-23
