ከተቀሰሰ አንድ አመት ሊሞላው ጥቂት ጊዜያት የቀሩት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ዛሬም ብዙዎችን እያፈናቀለ ፤ መሰረተ ልማቶችን እያወደመ እንዲሁም ንጹሀንን እየሰዋ ቀጥሏል ።
ከጅምሩ አንስቶ እስከዛሬዋ ዕለት ከሩሲያ በተቃራኒ የቆሙት ምዕራባዊያን በሩሲያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦች መጣሉን ተያይዘውታል ። አሁንም የአውሮፓ ፓርላማ የሩሲያ ኃይል በዩክሬን ጦርነት አሰቃቂ ድርጊቶችን ፈጽሟል በማለት የሽብር ድጋፍ ሰጪ ሀገር ሲል መፈረጁ ተሰምቷል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ያሉ ሆስፒታሎችን ፣ ትምህርት ቤቶችን ፤ የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮችና መጠለያዎች ላይ ወታደራዊ ጥቃት በመሰንዘር ብሎም የሰብዐዊ መብት ረገጣዎች አለም አቀፋዊ ሕግን ጥሳለች ያለው ፓርላማው የሽብርተኝነት ደጋፊ የሚል ፍረጃ ለመስጠቱ እንደ ምክንያትነት አንስቷቸዋል።
ይህ ውሳኔ የአውሮፓ ህብረት ሀገራትን የሽብርተኝነት ድጋፍ ሰጭ ብሎ የሚፈርጅበት የህግ ማዕቀፍ የለውም በሚል ትችት አስተናግዷል ። ነገር ግን ውሳኔውን 494 የምክር ቤቱ አባላት የደገፉት ሲሆን 58ቱ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል። 27ቱ የአውሮፓ ህብረት ሀገራትም ይህን እርምጃ እንዲከተሉ ውሳኔ ተላልፏል።
የሁለቱ ወገን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሩሲያን ጎጂ ዩክሬንን ተጎጂ አርጎ በመውሰድ በሩሲያ ላይ የማዕቀብ ናዳ ሲያወርዱ የከረሙት ምዕራባዊያን ዩክሬን በሩሲያ ላይ ያደረሰቻቸውን ውድመቶች አይናቸውን ገልጠው ለማየት ተሰኗቸዋል ።
ዩክሬን ለሞስኮ ድጋፍ የሚያደርጉ ቀሳውስት አሉበት ባለቻቸው ገዳም ላይ ጥቃት ማድረሷ በዚህ ሳምንት ውስጥ በሰፊው የተዘገበ ጉዳይ ቢሆንም የአውሮፓ ፓርላማ ይህን ድርጊት ከማውገዙ በፊት ሩሲያን ሽብርተኛ ብሎ መረጅ ቀዳሚ ተግባሩ ማድርጉ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል ።
ሩሲያ ላደረሰችብኝ ጥቃት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአሸባሪነት ያውጅልኝ በማለት ስትወተውት የነበረችው ዩክሬን በአውሮፓ ህብረት ውሳኔ መደሰቷን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል ።
ዓለም ሩሲያን ከሁሉም ነገሮች በማግለል በዩክሬን ንጹሀን ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ሁሉ ተጠያቂ እንድትሆን ሊያደርግ ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሜሪካና ሌሎች ሀገራትም ሩሲያ የሽብር ድጋፍ ሰጪ ሀገር መሆኗን ሊያውጁ ይገባል ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-11-24
