በተለያዩ ሀገራት በሚደርሱ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮዓዊ አደጋዎች ምክንያት በሰው ልጅ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል እና ለመቀነስ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይመሠረታሉ።
ከእነዚህ ተቋማት በዋናነት ከሚጠሩ እና በተባበሩት መንግሥታት ሥር ያለው የዓለም የምግብ ፕሮግራም አንዱ ነው። የተመሠረተው በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1954 ከ 60 ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት ነበር።
ዋና መሥሪያ ቤቱ በጣሊያን ሮም ከተማ የሚገነው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዓላማ በርሀብ አደጋ የሚሞቱ ሕዝቦችን መታደግ እንደኾነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዓለማችን በቂ ምግብ ከማያገኙ ዜጎች 11% የሚኾኑ ዜጎችን የመርዳት ዓላማ ይዞ እየሠራ ነው።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በአጭር ስያሜው (WFP) ከተመሰረ ከ1ዓመት በኋላ የመጀመሪያ የድጋፍ በሰሜን ኢራቅ ቦኢን ዛህራ በተባለ አካባቢ 12 ሺ ሰዎች በሞቱበት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ላይ ነበር።
ለተጎጂ ሰዎች 1500 ሜትሪክ ቶን ስንዴ270 ቶን ስኳር ድጋፍ በማድረግ ሥራውን ጀመረ። ይህ የድጋፍ ሥራውም ቀስ በቀስ ዓለምን ማዳረስ ጀመረ።
ዓለማችን የርሀብ ወሬ እንዳይሰማባት ማድረግ ፣ የምግብ ዋስትና ሙሉ ለሙሉ የተጠበቀ እንዲኾን ማድረግ፣ አስተማማኝ የግብርና ሥራ በሀገራት እንዲኖር ማድረግ ደግሞ ተቋሙ ማሳካት የሚፈልገው ትልቁ ግብ እንደኾነ በተቋሙ ታሪክ ላይ የተጸፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የተቋሙ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ 36 ሀገራትን ያቀፈ ነው። የምርጫቸው ሒደር ገሚሶቹ በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ እና ማኀበራዊ ካውንስል የሚመረጡ ሲኾን ገሚሶቹ ደግሞ በዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ፋኦ ይመረጣሉ።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ 120 በላይ ሀገራትን በማዳረስ ከ128 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ሰዎች ዕርዳታ አድርጓል። በኢትዮጵያም ቢኾን ከፍተኛ የድጋፍ ሥራዎን በመስራት ይታወቃል። ተቋሙ በይፋዊ መካነ ድሩ ባሰፈረው መረጃ በኢትዮጵያ በጦርነት በድርቅ ሳቢያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ 20.4 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እርዳታ የሚሹ እንደኾነ ይገልጻል።
በተያዘው ዓመት ከተጠቀሰው ቁጥር ውስጥ 2.9 ሚሊዮን ለሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ርሀብን ለመታገል በሚያደርገው ጥረት፣ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ለዜጎች ምቹ ኹኔታ እንዲፈጠር በማድረግ እንዲሁም ርሀብ የጦር መሣሪያ እንዳይኾን በመከላከሉ ረገድ በሰራቸው ሥራዎች ከሁለት ዓመት በፊት የኖቤል የሠላም ሽልማትን አግኝቷል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-11-24
