ማር ሲባል አምራቿ ንብ መሆኗ ትዝ ይለናል፤ ከጉንዳንም ማርን የሚያመርት ዝርያ መኖሩን ያውቁ ኖሯል? ባለ ብዙ ዝርያዎቹ ጉንዳኖች በስራ ትጋት ስማቸው የሚጠቀስ ነፍሳት መሆናቸው ይታወቃል።
በርግጥ ከንብ ሌላም አበባዎችን ወደ ጣፋጭ ፈሳሽነት የመቀየር የተፈጥሮ ስጦታው ያላቸው ነፍሳት ቢኖሩም ከጉንዳን ዝርያ አበቦችን ወደ ማር የሚቀይር መኖሩ ግሩም ነው ይላሉ በዘርፉ ላይ የሚጽፉ ሰዎች።
ሃኒፖት የሚሰኙት ማር አምራች የጉንዳን ዝርያዎች በልዩነት በዚህ ተግባር ላይ የተካኑ ናቸው። ለጉንዳን ስብስቡ የመኖር ቋትም ናቸው፤ የምግብ እጥረት ሲያጋጥም መንጋውን በዚሁ ተፈጥሯዊ ጥበባቸው ይታደጋሉ።
እነዚህ ልዩ ስራ ያላቸው ጉንዳኖች ግን ተንቀሳቅሰው አበባ የሚቀስሙ አይደሉም። ይልቁንም ይሄንንው ማር ለማምረት የሌሎች ጉንዳኖች እገዛ ያስፈልጋቸዋል።
ሰራተኛ ጉንዳኖች ለነዚሁ ባለ ልዩ ስራ ጉንዳኖች ጣፋጭ የአበባ ክፍሎችን ሰብስበው ያመጡላቸዋል። እነዚሁ ለጉንዳኖች የማር ገንቦ የሆኑት ሃኒፖት ጉንዳኖች ሆዳቸው ጣፋጩን ፈሳሽ ማምረት እስኪችል ይመገባሉ። ከዚያም ጣፋጩን የጉንዳን ማር ያመርታሉ።
መንጋው የምግብ እጥረት ወደማጋጠሙ ሲያመራም ይሄው የማምረት ሂደት በሃኒፖት ጉንዳኖቹ ይታደሳል። የእነዚህ ማር አምራች ጉንዳኖች ሆድ ተለቅ ያለ መሆኑም መንቀሳቀስ ቀላል ስለማይሆንላቸው ለአደጋ ያጋልጣቸዋል።
እነዚሁ የጉንዳን ዝርያዎች ለጉንዳኖች መንጋ አስፈላጊ ሀብቶች ከመሆናቸው ጋር በተያያዘም አንዱ የጉንዳን መንጋ ሌላኛውን ሲያጠቃ እነዚህን ማር አምራች ጉንዳኖች ሰርቆ የራሱ ያደርጋል።
ከንብ ማር ጋር የእነዚህ ጉንዳኖች ማር ተመሳሳይነት ቢኖረውም፤ በጣፋጭነት ግን ለሰዎች ከንብ ማር የበለጠ ጣፋጭነት የለውም ሲል ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል። በንጥረ ነገር ክምችቱም ቢሆን ከንብ ማር የተለየ ይዘት ኖሮታል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-24
