ሀገሬ ቲቪ

ጀርመን እና ጃፓን የፀረ-ኮሚንዝምን ፊርማ ተፈራረሙ

ሕዳር 16 1929 ዓ.ም. ከ86 ዓመታት በፊት፤ በበርሊን ሁለት አካላት ከጠረጴዛቸው ላይ የተቀመጠውን ወረቀት በየተራ ፈረሙ።

ኋላም ብርጭቋቸውን አጋጭተው መጪው ግዜ ይተነብዩ ገቡ። ነገሩ ዛሬ ዓለም የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጥንስስን ያየበት ነው።

በምስራቁ ጫፍ ያለችው ጃፓን ከምዕራቡ ዓለም የዚያን ግዜ ግዙፍ ጦረኛ ጀርመን ጋር ያደረጉት ህብረት ነበር። ስምምነቱን አንቲ ኮሚናል (የፀረ-ዓለማቀፋዊ ኮሚንስትነት) የሚል ነበር።

ስያሜው ለስምምነቱ ሽፋን ይሁነው እንጂ የግዜ የጀርመኑ መሪ አዶልፍ ሂትለር ፍላጎት ግን ሶቭየት ህብረትን ያነጣጠረ ነበር።

ነገሩ በርከት ያሉ ምክኛቶች ቢመዘዙለትም ዋነኛው ኝ ይህነው ይላሉ የታሪክ ባለሙያዎቹ። በዚያው ዓመት ቀደም ብሎ ቻይና እና ሶቪየት ህብረት ያደረጉት ጥቃትን በጋራ የመከላከል ስምምነት ጃፓንን ያንገበግባት ይገባል።

ቀድሞውንም ወደ ምስራቅ የመስፋት እቅድ በልቡ የነበረው ሂትለር ነገሩን ለፕሮፖጋንዳነት ተጠቀመበት። በዚያም ሳቢያ የሩቅ ምስራቋን ሀገር ዋነኛ አጋር አደረጋት።

በግዜው ዓለምን ኮሚኒስት ሊያደርጉ ነው ቀድመን ልንከላከለው ይገባል ሲል ወዳጆችን ሲፈልግ ለነበረው ሂትለር እፎይታን የሰጠ ነበር።

በግዜው ከአውሮፓውያኑ ወገን ቢጤውን ፍለጋ ሲዳክር ለነበረው ሂትለር የፋሽስቱ ቤኖቶ ሞሶሎኒ ሌላኛው ወዳጁ ነበር።

ሂትለር ከጃፓን ጋር ከመፈራረሙ ዓመት ቀደም ብሎ ከሞሶሎኒ ጋር ተቀምጠው ሀሳቡን መክረውበት ነበር። ሂትለር ከጃፓን ጋር ውል እንዳሰረ የሶቭየትን መሬት ይሰረስር ገባ።

ሶቪየት ሕብረትም ደጋግማ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ታስጠነቅቅ ገባች። ከሦስት ዓመት በኋላ ዓለም ዳግም ለሁለት ተከፍላ ትፋለም ጀመረች። ዓለም ዳግም በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሰው ልጆችን ገበረች።

ሁሉም በዛሬው ዕለት በወረቀት ላይ በዋለው ፊርማ አንድ ብሎ መቁጠሩን የጀመረው የዛሬ 86 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ሆነ።

በሳምሶን ገድሉ
2022-11-25