ሀገሬ ቲቪ

አዝናኙ የባቡር ጣቢያ ጠቋሚ ወጣት

ከሰሞኑ የማህበራዊ መዝናኛ መድረኩን አንድ በኳታር ያለ ወጣት ተንሸራሽሮበታል።

ዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ እድሉን ገና ስታገኝ እንዴት ተደርጎ ያሉ ሁሉ በኳታር እጃቸውን በአፋቸው ጭነው መገረሙን ቀጥለዋል።

ኳታር እግር ኳስ ጨዋታውን ብቻም አይደለም ያዘጋጀችው፤ ሌሎች ሊታዩልኝ ይገባል ያለቻቸውንም ስፍራዎች በሚገባ አዘጋጅታቸዋለች።

ታዲያ ቀልብን ቆንጠጥ የሚያደርጉት ዘመናዎዎቹ የባቡር መጓጓዣዎች ከስታዲየሞቹ ባሻገር ወደ እነዚህ ታሪካዊ ቦታዎችም ጭምር ያደርሳሉ።

መቼም የሰው ሀገር ነው እና ያሉት ገበያም ይሁን ስታዲየም ቆይተው ሲመለሱ የባቡር ጣቢያ ጠፍቶቦት እንዳይደናገሩ ኳታር አንድ መላን ዘይዳ ነበር፤ አቅጣጫ የሚጠቁሙ ሰዎችን በስታዲየሞቹ ዙሪያ ማኖር።

ታዲያ ከእነዚህም አንዱ የሆነው ኬኒያዊ የ23 ዓመቱ አቡበከር አባስ ጨዋታ በታከለበት መንገድ ስራውን መስራቱ የበርካቶችን ቀልብ አሸፍቷል።

በኳታር ካሉ ታሪካዊ ቦታዎች አንዱ ሱቅ ዋቂፍ ይሰኛል በዚህ አቅራቢያ የሜዳ ቴኒስ በሚዳኝበት ዘለግ ያለ ወንበር ላይ ተቀምቶ እጁ ላይ በሌባ ጣቱ የሚጠቁም ከፍ ያለ እጅ መሳይ ነገር አጥልቆ በሙዚቃ አቅጣጫየሚተቁም ወጣት አለ።

እሱ ነው ኬኒያዊው አባስ ማለት። አቡበከር አሁን በማህበራዊ መድረክ ላይ ዝነኛ ሆኗል። የዓለም ዋንጫውን ለመታደም ወደኳታር ያቀና ሁሉ እሱ ያለበትን ለመርገጥ ይጣደፋል።

“በቲክቶች ላይ ተመልክቼው ነው ላየው የመጣሁት። በጣም ዘን አያደርጋል። ስራው ቀላል ይመስላል ግን ሰዉን ተመልከተው። በስራው በጣም በጣም ዘና እያለ ነው ያለው።”

ታዲያ አባስ በስራው ላሳየው ትጋት እና ሰዎችን የበለጠ ማስደሰት በመቻሉ ከቀጣሪው ኩባንያ ስጦታዎች ተበርክተውለታል።

የአባስ ዘና ያለ መንገድ አሁን በሁሉም የባቡር ጣቢያ መንገድ መሪዎች ዘንድ የተወደደ ይመስላል።

በየትኛውም ጥግ ይሂዱ የባቡር ጣቢያውን አቅጣጫ ጨዋታ በሞላበት መንገድ የሚያሳዩ ወጣቶች እርሶን ወደ መዳረሻዎት ይመራዎታል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-11-25