አቢሲኒያ ባንክ በሀገሪቱ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስራዎቹ ላይ ተጽዕኖ ቢያሳድሩበትም ካለፈው የሂሳብ ዓመት አንጻር የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጿል ።
በ 2021/22 የሂሳብ ዓመት ካለፈው ዓመት አንጻር 127 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ያልተጣራ 4.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት ችያለሁ ያለው ባንኩ በዚህም አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 149.4 ቢሊዮን ብር ማድረሱን አስታውቋል ።
በተጠናቀቀው ሂሳብ ዓመት የብድርና ቅድመ ክፍያዎች መጠን 113.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያስታወቀው ባንኩ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የሰጠው ብድር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ48 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቁሟል ።
ባንኩ በተጠናቀቀው ሂሳብ ዓመት ያቀዳቸውን አብዛኞቹን ግቦች ማሳካት የቻለ ቢሆንም በሀገሪቱና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶች ሳቢያ ማስገባት የቻለው የውጪ ምንዛሬ ከአምናው መጠኛ ቅናሽ ማሳቱ ተገልጿል ። በቀጣይም የውጪ ምንዛሬ ገቢውን ለማሳደግ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱን የላቀ ደረጃ ለማድረስ ከ ቪዛ ካርድ ጋር በመተባበር አዲስ ካርድ የሚያወጡ ባለእድለኛ ደንበኞችን ወደ ኳታር ለመላክ የጀመረውን ዘመቻ በማጠናቀቅ አራት እድለኛ ደንበኞችን ሙሉ ውጪ በመሸፈን ወደ ኳታር የሚበሩበትን ቲኬት አስረክባል።
በዮሴፍ ከበደ
2022-11-28
