ሀገሬ ቲቪ

የዝንጀሮዎች የምግብ ፌስቲቫል

መቼም ሁሉም እንደሚኖርበት አካባቢ የተለያየ ወግ እና ሰርዓት አለው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ምክንያት ተሰፍሮላቸው የሚደረጉ አስገራሚ የአደባባይ ፌስቲቫሎችን እናውቅ ይሆናል።

ታዲያ ዛሬ ሰዎች ሳይሆኑ ጦጣዎች ዘና የሚሉበት የዓደባባይ በዓል ባለቤት መሆናቸውን ሰማን እና ልናጋራችሁ ወደድን።

ነገሩ በታይላንድ ሎፕቡሪ በምትባል ጥንታዊት ከተማ የሚከወን ተግባር ነው። ይህ ፌስቲቫል ዘንድሮ 43ተኛ ዓመቱን መድፈኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ያወጋሉ።

ታዲያ ጦጣዎቹ በአካባቢው ውድ ናቸው የሚባሉ ምግቦች ቀርበውላቸው እንዳሻቸው እያድፋፉ ይመገባሉ። በዚያን ዕለት ማለዳ የከተማው አውራ ጎዳና ለተሽከርካሪዎች አስቸጋሪ ነው።

“ከዚህ በፊት ከ300 የማይበልጡ ጦጣዎች ነበር የነበሩት አሁን ቁጥራቸው ጨምሮ 4 ሺሕ ደርሰዋል። ከተማዋ የጦጣ ከተማ ተብላ ነው የምትታወቀው። ዝንጀሮዎች እና ሰዎች በመተሳሰብ የሚኖሩበት ነው። ጦጣዎች አንዳንዴ ሊረብሹ ይችላሉ ይህ ግን ባህርያቸው ነው።”

ፌስቲቫሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ከ43 ዓመታት በፊት ቱሪስቶችን ለመሳብ እና ከጦጣዎቹ ጋር ሰላማዊ የሆነ ግንኙነትን ፍለጋ ስለመጀመራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የፌስቲቫሉ ባለቤቶች የሆኑት ጦጣዎቹ በሰው እጅ ተቀርፀው በቆሙት አስተናጋጅ የጦጣ ሀውልቶች ላይ እየተንጠላጠሉ ያሻቸውን ይመገባሉ።

በዓመት አንዴ የሚከወነውን ይህንን ፌስቲቫል ለመታደም በቦታው የሚገኙ ቱሪስቶችም ቢሆኑ አይቀርላቸውም ጦጣዎቹ አንዴ አናታቸው ላይ ከዚያም ወደ ትከሻቸው እየተዘዋወሩ እንዳሻቸው ይፈነጫሉ።

“ደንግጫለው ሰዎች ጦጣዎችን ሲመግቡ ሳይ ምን ሆነዋል ብዬ ነበር።”

ዘንድሮ ፌስቲቫሉ ከኮቪድ ቫይረስ እቀባ በኋላ የተደረገ በመሆኑ ጦጣዎች ለጦጣዎች የሚል ስያሜን ተሰቶታል። ከተማዋ እየጨመረ በመጣው የጦጣዎች ቁጥር የተጨናነቀች ናት።

በከተማዋ ያሉ ነዋሪዎችም ቢሆኑ ማልደው ቁርሳቸውን ተመግበው ወደ ዕለት ተግባራቸው ሲሰማሩ እነዚህን ጦጣዎች መመገብን አይዘነጉም።

የሱቅ ባለቤቶች ሱቃቸውን ሲከፍቱ ጦጣዎቹን ከመገቡ በኋላ ዳግም ወደ ሱቆቻቸው መጥተው እንዳይረብሿቸው የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ። በበራቸው ላይ በአስፈሪ የዱር አራዊት አምሳያ የተሰሩ አሻንጉሊቶችን ማስቀመጥ። ጦጣዎቹም ቢሆኑ እጃቸው አያርፍም የከተማዋን ያገኙትን ማበላሸት እና ማድፋፋት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው።

የአካባቢው ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የጦጣዎችን መራባት ለመቀነስ የተለያዩ መንገዶችን በመከተል ላይ እንደሆነም ይናገራል።

ነዋሪዎቹ ግን ይህ ሁሉ ነገር ቢያማርራቸውም ከጦጣዎቹ ጋር ያላቸውን አኗኗር ይወዱታል። ካላቸው ላይ ቀንሰው ጦጣዎቹን መንከባከባቸውን አላቋረጡም እና።

በሳምሶን ገድሉ
2022-11-29