ሀገሬ ቲቪ

የማይክል ጃክሰን ተወዳጅ አልበም

ማይክል ጃክሰን የፖፕ የሙዚቃ ስልት ሲነሳ ስሙ በክብር የሚነሳ የሙዚቃ ሰው ነው። የፖፕ የሙዚቃ ንጉስ የሚለው ክብርም ከስሙ ላይ ተደርቦለታል።

ሙዚቃን ከዳንስ ባጣመረ ክህሎቱም የዳንስ ማሽን ተብሎም ይጠራል። በሙዚቃው ዓለም፣ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት እና ክብርን ያተረፈው ማይክል ጃክሰን ስምንተኛው የግራሚ ሽልማትን ያገኘበትን አልበሙን ትሪለርን ለአድማጮች ጆሮ ያደረሰው በዛሬዋ ዕለት በ1975 ዓ.ም. ነበር።

ይሄው አልበሙ በዓለማችን ከፍተኛ ሽያጭ እና ተወዳጅነት ካገኙ ቀዳሚዎቹ አልበሞች አንዱ ነው። ለብዙ ጊዜያትም ከወጣበት ጊዜ ጀመሮ የዓለማችን ከፍተኛ ሽያጭ ካስመዘገቡ አልበሞች የአንደኝነቱን ስፍራ ይዞ ቆይቷል። እስከዛሬም ቢሆን ከቀዳሚዎቹ አናት ከሚሰለፉ የአልበም ስራዎች መካከል አልጠፋም።

የዓለማችን የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ዕውቅ አዝናኝ፣ ድምጻዊ፣ የሙዚቃ ግጥም ጸሐፊ ብሎም የወጣለት ዳንሰኛ የኾነው ማይክል ጃክሰን የተወለደው በአሜሪካ ኢንድያና በ1950 ዓ.ም. ነበር። አባቱ ጃክሰን ጃክሰን ፋይቭ (Jackson 5) ብሎ ካቋቋመው የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ትንሹ እና በጣም አቅም ያለው እርሱ ነበር። ከአምስት ወንድሞቹ ጋርም ነበር በዚህ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ይጫወት የነበረው።

ኋላም በጃክሰን ፋይቭ የልጆቹ የሙዚቃ ክህሎት የሞቶውን ሪከርድስ ፕሬዝዳንት ቤሪ ጎርዲ ተማርኮ ከተፈራረሙ በኋላ ለጃክሰኖች ስኬት ሩቅ አልሆነችም። በ1960ዎቹ በፖፕ ስልት ከቀዳሚዎቹ መሰለፍ የቻሉ ስራዎችንም አበርክተዋል። ከነዚ ስራዎቻቸውም ‘’I want you back’’ እና ‘’I will be there’’ ይጠቀሳሉ።

በስራዎቻቸው ተወዳጅነትን ማትረፍ ያልተሳናቸው ጃክሶኖች ከሞቶውን ሪከርድስ ጋር ከተለያዩ በኋላ እነርሱም በየግላቸው ወደ መስራቱ አዘንብለዋል። በዚህ ውስጥ ማይክል ጃክሰን በግሉ ተወዳጅ መሆንም ችሏል።

ሙዚቃን ከዳንስ አጣምሮ የሚዋጣለት ማይክል ጃክሰን ከአልበም ስራዎቹ ደግሞ ከ40 ዓመታት በፊት ያወጣው ትሪለር ከፍተኛ ተወዳጅነትን አስገኝቶለታል።

ይሄው አልበሙ በዓለም ዙሪያ 50.2 የተመዘገበ ሽያጭ ያስመዝገበ ሲሆን 110 ሚሊዮን ኮፒ ሽያጭ እንዳስመዘገበም ይገመታል። በታሪክ ትልቅ ሽያጭ ከያዙ አልበሞች ከቀዳሚዎቹ ይሰለፋል።

በዚህ አልበሙም ስምንተኛው የግራሚ ሽልማትን የተቀዳጀበት ሲሆን፣ የፖፕ የሙዚቃ ንጉስ የሚል ስያሜንም ማግኘት ሩቅ አልሆነበትም። በ1970ዎቹ አጋማሽ ይሄንንው የንግስና ስያሜ ተቀዳጅቶታል። በሚሰራቸው የሙዚቃ ቪዲዮችም ቢሆን ስራዎቹ የዓለም አቀፍ ተመልካችን ትኩረት መሳብ የቻሉ ናቸው።

የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሙዚቃ መልክ እስከመሆን የደረሰው ለሙዚቃ የተሰጠው ማይክል ጃክሰን በ2001 ዓ.ም. በ50 ዓመቱ ቢያርፍም ስራዎቹ ዛሬም ተደማጭ ናቸው። ትሪለር አልበሙም ቢሆን ከተወዳጅ እና ከፍተኛ ሽያጭ ካላቸው አልበሞች ከቀዳሚዎቹ እንደተሰለፈ ነው።

በአብርሃም በለጠ
2022-11-29