ሀገሬ ቲቪ

የዓለማችን ውዱ መድኃኒት

መቼም ሰው ኾኖ ከበሽታ የሚያመልጥ የለም። ቀለል እና ከባድ በሚባሉ ሕመሞች የሰው ልጅ ይፈተናል። በሕክምና ዘርፉ የሚሰጡ የተለያዩ መድኃኒቶች ደግሞ ከሕመሙ እንዲያገግም ይረዱታል።

ዛሬ በዓለማችን ውድ እና እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ሊጠቀሙት ስለሚችሉት አንድ መድኃኒት ለንነግራችሁ ነው። የማይቆም የደም መፍሰስ ወይም በሳይንሳዊ አጠራሩ ሄሞፊሊያ የሚባል ሕመም አለ።

ሄሞፊሊያ ወይም የደም አለመርጋት ችግር የሚከሰተው ፋክተር 8 አሊያም ፋክተር 9 የተሰኙ እና ደም ጤናማ በኾነ መንገድ እንዲረጋ የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን በበቂ መጠን ሳይኖሩ ሲቀር የሚፈጠር ነው።

ለዚህ ህመም የሚኾን አንድ መድኃኒት ታዲያ 3.5 ሚሊየን ዶላር ወይም ደግሞ ከ178 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ዋጋ መቅረቡ ተሰምቷል።

ሄምጄኒክስ የተሰኘውን ይህን መድኃኒት የአሜሪካ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር መድኃኒቱን ፈትሾ እና አረጋግጦ ለገበያ መቅረብ ይችላል ሲል ይሁንታውን ሰጥቷል።

ሄምጄኒክስ የተሰኘው መድኃኒት ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ ቢኾንም ዋጋው ግን አደለም የሚቀመስ የሚታሰብም አልኾነም።

ሄሞፊሊያ ለሚሰቃዩ ሰዎች የተለመደው ሕክምና ተከታታይ መርፌዎችን በመወጋት ነው ሕመማቸውን የሚያስታግሱት።

3.5 ሚሊየን ዶላር ወይም ደግሞ ከ178 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣውን መድኃኒት አቅም ያለው ቱጃር ካልኾነ ለደኃው የሚኾን አይደለም ስለዚህ መመረቱ ምን ዋጋ አለው ብዙኃኑን ካልጠቀመ የሚል ስሞታዎች ከዚም ከዚያም እየተወረወሩ ነው።

ነገር ግን ሄሞፊሊያ ወይም የደም አለመርጋት ችግር በዘር የሚተልለፍ እንደመኾኑ ዘረ መል ላይ የሚደረጉ ሕክምናዎች ደግሞ ጥልቅ በመኾናቸው መድኃኒቶች በእጅጉ ውድ እንዲኾኑ አድርጎአቸዋል ሲል ኦዲቲሴንትራል አስነብቧል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-11-30