ሀገሬ ቲቪ

የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት አሁንም አሳሳቢ ሆኗል ተባለ

ኤች አይቪ ኤድስ መከሰቱ ከተሰማ ከ3 አስርት አመታት በፊት ጀምሮ ያስከተለው እልቂት ብሎም የስነለቦና ጫና አለማችንን በከፍተኛ ሁኔታ ፈትኗታል።

ይህ ቫይረስ ሀገራችንም ላይ ከፍተኛ እልቂት ያደረሰ ሲሆን ሁሉም አካል ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረትና በተደረገ ርብርብ የቫይረሱ የመሰራጨት አቅምን በተወሰኑ መልኩ ለመቀነስ ተችሏል።

ታዲያ አሁን ላይ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ኤች አይቪ ጠፍቷል በሚል እሳቤ በታዩ መዘናጋቶች ቫይረሱ በድጋሜ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጤና ሚኒስተር በየዐመቱ ህዳር 21 የሚከበረውን የአለም ኤች አቪ ኤድስ ቀንን አስመልክቶ ባዘጋጀው መድረክ ላይ አስታውቋል።

በሀገራችን የቫይረሱ ተጠቂ ከሆኑ ዜጎች ውስጥ 62 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን የጠቆሙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ሊያ ታደሰ በ 2014 ምርመራ ካረደጉ ሰወች መካከል ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰወች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።

ይህ ቁጥር አሳሳቢ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ በይበልጥም በሀገራችን የተከሰቱ የሰላም መደፍረሶች ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተያዘውን ዕቅድ እንደፈተኑት እና ሊታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ ሀገር የቫይረሱ የመሰራጨት መጠን 0.93 በመቶ ላይ ቢገኝም ይህ ቁጥር ከቦታ ቦታ እንደሚጨምር ተናግረዋል ። ከሀገራችን ከተሞች ጋምቤላ በከፍተኛ ሁኔታ ቫይረሱ የሚሰራጭባት ሀገር እንደሆነችም ተጠቁሟል።

ቫይረሱ በጋምቤላ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር የቻለበት ምክንያት ምን ይሆን ስንል የጠየቅናቸው የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮሆት ጋትዊች በአካባቢው ያሉ አንዳንድ ባህሎችን እንደ ምክንያት አንስተዋል።

ቫይረሱ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ40 ሚሊየን በላይ ሰወችን የገደለ ሲሆን 38 ሚለየን ሰወች በደማቸው ይገኛል። በኢትዮጵያም 617 ሺ 921 ሰወች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ተገልጿል።

የዘንድሮ የአለም የኤድስ ቀን ፍትሀዊና ተደራሽ የኤች አይቪ ኤድስ አገልግሎት ለሁሉም በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል።

በዮሴፍ ከበደ
2022-12-01