የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚዳስ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህ ሰነድ ተፈናቃዮች የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተመለከቱ መረጃዎች ተካተውበታል በተጨማሪ በዚህ ኮሚሽኑ ባደረገው የክትትል ሥራ የሀር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃን አስመልክቶ ያገኛቸውን መሠረታዊ ክፍተቶች እንዳሉ በተቋሙ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና የፍልሰተኞች መብቶች የሥራ ክፍል ዳይሬክተር የኾኑት ወ/ሮ ዕንጉዳይ መስቀሌ ተናግረዋል።
በተለይም የተፈናቃዮች ምዝገባና ሰነድ የማግኘት ሥርዓት ላይ የተስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል።
ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስለማድረግ የሚያትተውን የካምፓላ ስምምነትን ኢትዮጵያ እንደምትቀበለው ተስማምታ ካጸደቀች በኋላ ተፈናቃዮቹን የተመለከተ ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ አላዘጋጀችም።
እንዲሁም ተቋማዊ አደረጃጀት የላትም። ይህም ታዲያ መፈናቀልን የመከላከል፣ ለተፈናቃዮች የሚደረጉ የጥበቃ እና ድጋፍ ሥራዎች እንዲሁም የዘላቂ መፍትሔ የማመቻቸት ሂደቱን እንዳስተጓጎለው ነው ወ/ሮ ዕንጉዳይ የሚናገሩት።
ልዩ ጥበቃ እና እንክብካቤ የሚሹ ሕፃናት ሴቶች አረጋውያን እና አካል ጉዳተኛ የሀገር ውስት ተፈናቃዮችን ልዩፍላጎት መሠረት ያደረገ የድጋፍ ሥራዎችም እንደሌሉ ነው ተቋሙይፋ ባደረገው ሪፖርት ያመላከተው።
የኢትዮጵያ ሰባዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሌሎች ጉዳዮችም ተመሳሳይ ሪፖርቶችን በስፋት ያወጣል። ሪፖርቶችን ይፋ ከማድረግ ባለፈ የሚሰራው ሥራ ምንድነው ስንል ጠይቀናል።
ኮሚሽኑ ዝግ ውይይቶችን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ከማድረግ አንስቶ አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድ የመወትወት ሥራን ይሠራል የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል።
ሪፖርቱ በድምዳሜው መንግሥት ተፈናቃዮችን የተመለከተውንና በሂደት ላይ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት በማጠናከር የተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች በበቂ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት እንደሚገባ ይጠቁማል።
በተጨማሪ የተፈናቃዮችን ጥበቃ እና ድጋፍ የሚያስተባብር ተቋማዊ መዋቅር መዘርጋት እንደሚገባ ይገልጻል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-12-01
