ኔቶ ለዩክሬይን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክራለሁ ከማለቱ በተጨማሪ የሩስያ ጎረቤት ሀገራትን እደግፋለሁ አለ።
ሩስያ በበኩሏ ወታደራዊ ህብረቱ የዩክሬይንን ጦርነት በፖለቲካዊ መፍትሄ የመቋጨት ፍላጎት እንደሌለው ማሳያ ነው ብላለች። በኒውክሌር ኃይሎች መካከል ወታደራዊ ግጭት እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስባለች።
የኔቶ አባል ሀገራት ባለስልጣናት ለሁለት ቀናት በሮማንያ መክረዋል። እነዚሁ ሀገራት ታዲያ ከሩስያ ጫና እየደረሰባቸው ነው ያሏቸውን የሞስኮን ጎረቤት ሀገራት እንርዳችሁ ብለዋል።
የኔቶ ዋና ኃላፊ ጀነራል ጀንስ ስቶልተንበርግ የወታደራዊ ህብረቱ አባል ያልሆኑት እና አጋር ተብለው ለሚጠሩት የሩስያ ጎረቤት ሀገራት ሞልዶቫ፣ ጆርጅያ እና ቦስንያ በሩስያ ጫና እየደረሰባቸው ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ጄነራሉ ድጋፍ እናድርግላቸው ባይም ናቸው። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም ከዩክሬይን ጉዳይ መማር ያለብን እነዚህን ሀገራት አሁኑኑ መደገፍ እንዳለብን ነው ብለው ተናግረዋል።
“የቦስኒያ፣ ጆርጅያ እና ሞልዶቫ ባለስልጣናት ተቀላቅለውናል።እነዚህ ሶስት የኔቶ ወሳኝ አጋሮች የሩስያ ጫና አለባቸው። የጋራ የደህንነት ስጋታችን ላይ፣ ወዳጅነታችንን ማጠንከር ፣ እድሳት ማድረግ፣ አቅም መገንባት እና በስልጠና የደህንነት እና መከላከያ ተቋሞቻቸውን አቅም ማሻሻል ላይ ተወያይተናል።”
የኔቶ ኃላፊው ጀንስ ስቶልተንበርግ በሌላ በኩል የኔቶን አባልነት የጠየቁት የፊንላንድ እና ስዊድን ጥያቄም ቢሆን ይሁንታ የማግኘት ሂደቱ ወደ መገባደዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
በውይይታቸው የኔቶ ባለስልጣናት አሁንም ቢሆን ለዩክሬይን የሚያደርጉትን ድጋፍ የማጠንከር ሃሳቡ አላቸው። ነዳጅም የጦር መሳሪያም ለዩክሬይን እናቀርባለን ባይ ናቸው።
የሩስያ ባለስልጣናት በበኩላቸው የወታደራዊ ህብረቱ ውይይት ውጤት አሁንም ቢሆን የዩክሬይንን ጦርነት ኔቶ በፖለቲካዊ መፍትሄ በውይይት የመቋጨት ፍላጎት እንደሌለው ማሳያ ነው እያሉ ነው።
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማርያ ዛክሮቭ ወታደራዊ ህብረቱ የዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ፍላጎቱ እንደሌለው ማሳያ ነው ብለዋል። የሞስኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ምዕራባውያን ዩክሬይንን አሁንም ከሩስያ ጋር እየተዋጋች እንድትቆይ ግፊት እያደረጉባት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
“በዩክሬይን ጉዳይ ካላቸው አቋም ጋር በተያያዘ ሳይቀር በኒውክሌር ኃይሎች መካከል ወታደራዊ ግጭት ሊኖር አይገባም። ግን ደግሞ ምዕራባውያን ዩክሬይን ከሩስያ ጋር የምታደርገውን ጦርነት ይበልጥ እንድታጠናክር እየገፏት ነው። “
ምዕራባውያኑ አሁንም ዩክሬይንን እየገፏት ነው ያሉት ሰርጌ ላቭሮቭ በኒውክሌር ኃይሎች መካከል ጦርነት የሚፈጠር ከሆነ ነገሩ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-12-01
