የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የስራ ፈጠራ ትምህርትን ለተማሪዎቻቸው የሚሰጡ ብቻ ሳይሆን፣ ራሳቸውም ስራ ፈጣሪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርም የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በሚፈጥሩት ስራ ራሳቸውን የቻሉ የሚሆኑበት አሰራር ላይ እየተመከረበት ነው ብሏል።
የሙያ እና ቴክኒክ ተቋማት ለተማሪዎቻቸው የስራ ፈጠራ ትምህርትን ከማስተማር አልፈው ራሳቸው ስራ ፈጣሪ በመሆን በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ይነሳል።
እየተከበረ ባለው የኢንተርፕሬነርሺፕ ሳምንት ላይ በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ ከዚህ በፊት እየሄድንበት የነበረውን አካሄድ በመቀየር የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የስራ ፈጠራ ትምህርትን ለተማሪዎቻቸው የሚሰጡ ከመሆናቸው ባሻገር ራሳቸውም ስራ ፈጥራን ባህል ያደረጉ የሚሆኑበት መንገድ ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑም ባላቸው ሃብት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ የሚያስችል ስርዓት ላይ ሊሰራበት እንደሚገባ እና ይህም ተጠንቶ ወደ ተግባር እንዲገባ እየተሰራ መሆኑን የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የጥናት እና ምርምር ዳይሬክተር ዶ/ር ሃብታሙ ሙሉጌታ ነግረውናል።
የሟ እና ቴክኒክ ተቋማት ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ታምኖበት ለተግባራዊነቱ ምክክር የተጀመረ ሲሆን በተቋማቱ ደረጃ ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ይሰራል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ተሻለ በሬቻ የሙያ እና ቴክኒክ ተቋማቱ በሚፈጥሯቸው ስራዎች ራሳቸውን ችለው በገቢ ከመንግስት ጥገኝነት እንዲወጡም እየተመከረበት መሆኑን ገልጸዋል።
በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እና በኢንተርፕሬነርሺፕ ዲቨለፕመንት ኢንስቲትዩት ትብብር የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት እየተከበረ ይገኛል።
በአብርሃም በለጠ
2022-12-02
