ሀገሬ ቲቪ

“ውሃ ጋር የተያያዙ ችግሮቻችንን በተገቢው ለዓለም ለማንጸባረቅ እየተሰራ ነው”

ሀገራችን ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውሃ ጋር የተያያዙ ችግሮች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተገቢው ለማሳየት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። በዓለም አቀፉ የኒው ዮርክ የውሃ ኮንፈረንስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብቁ የውሃ አጀንዳዋን ይዛ እንድትቀርብ ተቋማት ሊተባበሩ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ ብትባልም ከውሃ ጋር የተያያዙ ችግሮች አላጧትም። ዛሬም ከ38 በመቶ በላይ የሀገራችን ህዝብ ንጹህ መጠጥ ውሃ በተገቢው ተደራሽ አልሆነም። የውሃ ፍላጎትን ለማንጸባረቅ ደግሞ አለም ዓቀፍ መድረኮች ጥሩ አማራጭ ናቸው።

በመጭው 2023 በኛው መጋቢት ወር የውሃ ኮንፈረንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሜሪካ ኒውዮርክ ይካሄዳል። ታዲያ ሀገራችን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በውሃ አጠቃቀማችን ዙሪያ ሊያነሱ የሚችሉትን ጥያቄ ለመመለስ ምን እያደረገች ይሆን? እያጋጠሟት ያሉትን የውሃ ችግሮች በተገቢው ለማሳየት ምን እየሰራች ነው?

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪው አቶ አበራ እንደሻው ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ ብትባልም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በድርቅ ጭምር ከፍተኛ ተጎጅ መሆኗን በማስረዳት የታችኖቹ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

የውሃ ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያግዙንን የቴክኖሎጂ እና የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም ማግኘት የሚያስችለንንም አጀንዳ ይዘን ለመቅረብ እየሰራን ነው ሲሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሀብታሙ ኢተፋ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አረንጓዴ ልማት ላይ የምንሰራውን ስራም መሸጥ የምንችልበት አማራጭ አለን ብለዋል። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አበራ ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ በተያዘለት ዓለም አቀፉ የውሃ ኮንፈረንስ እንደሀገር አንድ አጀንዳ ይዞ ለመቅረብ ለመቀረብም በቀጣዮቹ ወራት ዝግጅቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚቀጥል ነግረውናል።

በአብርሃም በለጠ
2022-12-05