ሀገሬ ቲቪ

የነዳጅ አዳዮች ማኀበር ተደጋጋሚ ጥያቄ

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኀበር አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚስተካከል የትርፍ ህዳግ የለንም እና ይስተካከልልን ሲሉ ጠይቀዋል።

ማኀበሩ በነዳጅ ርክክብ፣ በዘይት ሽያጭ የመሳሰሉ ጥያቄዎች ቢኖሩትም ብዙ ጊዜ የሚነሳው ጥያቄ እና እስካሁን ያልተፈታው ጥያቄ ትርፍ ሕዳግ ነው ይላሉ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኀበር የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ የኾኑት በሱፈቃድ አማረ።

እስካሁን ከአንዲ ሊትር 23 ሳንቲም ብቻ ነው እያተረፍን ያለንው ብለዋል። የነዳጅ ዋጋ ጨምሮም ነዳጅ አዳዮች የሚያገኙት ያልተጣራ ትርፍ ከአንድ ቦቴ 10 ሺህ ብር ብቻ ነው።

በፊት ላይ ከአንድ ቦቴ መኪና 45 ሺህ ሊትር ነዳጅ ለማውረድ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ያስፈልግ ነበር አሁን ላይ ግን ከ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይኾናል። ወጪው ጨምሮ አሁንም ትርፋችን 10 ሺህ ብር ነው ሲሉ አቶ በሱፈቃድ ተናግረዋል።

የትርፍ ሕዳጉን የሚያወጣው መንግሥት እንደመኾኑ እንዲያስተካክልንን ብንጠይቅም እስካሁን መፍትሔ እንዳላገኙ አቶ በሱፈቃድ ገልጸዋል። የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ የትርፍ ሕዳጉ ግን ባለመስተካከሉ በዚህ የሥራ ዘርፍ መቀጠል አዳጋች ኾኗል።

አሁን ላይ ማኀበሩ የትርፍ ሕዳጉ ከ 23 ሳንቲም ወደ 1ብር 25 ሳንቲም ከፍ እንዲልለት ለመንግሥት አስታውቋል። በጉዳዩ ላይ ምልሽ እንዲሰጠን የጠየቅነው የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን፤ የማኀበሩን ጥያቄ እያጠናሁ ነው የትርፍ ህዳጉን ስወስን አሳውቃለሁ የሚል ምላሽ ሰጥቶናል።

ሀገር አቀፍ ደረጃ ከ 1 ሺ 100 በላይ ነዳጅ አዳዮች ያሉ ሲኾን 250 በላይ ወረዳዎች ደግሞ ነዳጅ ማደያ እንደሌላቸው ሰምተናል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-12-06