ሀገሬ ቲቪ

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ ከባድ ችግር ያጋጥመዋል

ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2022 በበርካታ ተግዳሮቶች ተተብትቦ ቆይቷል። የኮቪድ19 ያደረሰው ተጸዕኖ፣ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የደረሱ ጥፋቶች እና ጉዳቶችን በዋናነት መጥቀስ እንችላለን።

በአምተርዳም ዩኒቨርስቲ የማክሮኢኮኖሚ ምሁር የኾኑት ሮኤል ቢትስማን የአለም ኢኮኖሚ ላይ ቀውስ እየጨመረ የመጣው ባለፉት ትቂት ዓመታት አይደለም ይልቁንስ ካለፈው 100 ዓመት ጀምሮ የሚመዘዝ ነው ሲሉ መናገራቸው ፍራንስ 24 ዘግቧል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንስርቶ እስካሁን ድረስ የዓለም ኢኮኖሚ መረጋጋት እንደተሳነው ነው ምሁሩ የተናገሩት። የዓለም ኢኮኖሚ እንዲያ ያለ ውስብስብ ነገር ውስት ገብቶ አይተን አናውቅም ሲሉ ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የተከሰተው የኮቪድ 19 ቫይረስ ኾድ የባሰውን የዓለም ኢኮኖሚ ይብስ እንዲወድቅ አድርጎታል።

በተለይ ሀገራት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸው ደግሞ የሸቀጦች ዋጋ ሰማይ እንዲነካ አድርጎታል። ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ሠራተኛ እንዲቀንሱ ተገደዋል።

ባንኮች የዋጋ ግሽበቱን ለመቋቋም ሲሉ የወለድ መጠናቸውን ከፍ እንዲል አድርገዋል። ይህን ማድረጋቸው ደግሞ የሀገር ውስጥም የወጪ ንግዶችም እንዲሁ እንዲጎዱ ኾነዋል።

በዓለማችን ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ቻይና የዜሮ ኮቪድ ፖሊስን እስካሁን ተግባራዊ በማድረጓ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን መጀመር አልቻሉም። ይህም የራሱን አሉታዊ ጉዳት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ አሳድሯል።

ወደ ቀድሞ የንግድ እንቅስቃአሴዋ እንድትመለስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ብትጠየቅም ከጤናዬ በላይ ምንም የለም በማለት ጆሮ ዳብ አያለች መስላለች።

የተለያዩ ማዕከላዊ ባንኮች ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ጊዜያዊ ሊኾን የሚችለው ኢኮኖሚው ወደ ቀድሞው ሁኔታ ሲመለስ ብቻ እንደሆነ አጥብቀው እየተናገሩ ባሉበት ወቅት ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሞቅ በረድ ሲል የነበው የሩሲያ እና የዩክሬን ሰጣ ገባ ወደ ጦር መማዘዝ ተለወጠ።

የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ከነርሱ አልፎ ያደጉትንም ኾነ በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በምግብ እና በኃይል ምርቶች ላይ ያሳደረው ጉዳት ደግሞ ከሁሉም ይልቃል።

እንደ ጅርመን እና ጣሊያን ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ድግሞ በዚህ ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የገቡ ሀገራት ናቸው። የኢኮኖሚ ውድቅት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ነው ባለሙያዎች የተነበዩት።

የእንግሊዝ ኢኮኖሚ እንዲሁ መሰነጣጠቅ ጀምሯል። በቅርቡ የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የንግድ እንቅስቃሴአቸው እንዲጠናከር ወደ ቻይና ማቅናት ብዙ ያስተቻቸውን ጉዞ ማድረጋቸው የሀገራቸው ምጣኔ ሀብት የሚያገገምበትን አማራጭ ለማግኘት ነበር።

እነዚህ ሁሉ ተደራራቢ እና ተያያዥ ችግሮች መፍትሔ ሳያገኙ ሥር እየሰደዱ በመሔዳቸው ነው ቀጣዩ 2023 ከባድ ይኾናል የተባለው።

በሙሉጌታ በላይ
2022-12-07