ሀገሬ ቲቪ

የአፍጋኒስታን የመጀመሪያ ተመራጭ ፕሬዝዳንት

ሰውዬው ሃሚድ ካርዛይ ይሰኛሉ። ለአፍጋኒስታን በምርጫ የተሾሙ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው። ለአስር ዓመታት ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

ታሊባን በአሜሪካ እና አጋሮቿ ትብብር ታሊባን ከስልጣን ከወረደ በኋላ፣ እኒህ ሰው ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ የገቡት በዛሬዋ ዕለት በ1997 ዓ.ም. ነበር። መጀመሪያ ላይ የምዕራባውያኑን ድጋፍ ያላጡት ካርዛይ ኋላ የአሜሪካን የአፍጋን ጣልቃ ገብነት መተቸታቸው አልቀረም።

በ1950 ዓ.ም የተወለዱት ካርዛይ አባታቸውም ሆነ አያታቸው በሀገሪቱ ቀደም ባለው አስተዳደር ውስጥ የአገልግሎት ድርሻው ነበራቸው።

የሶቭየት ድጋፍ ካለው መንግስት ጋር ስምምነት ስላልነበራቸው በ1970ዎቹ የካርዛይ ቤተሰብ ወደ ፓኪስታን ተሰደዋል። ከህንድም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ1970ዎቹ አጋማሽ አግኝተዋል።

በአፍጋን ጦርነት ከሙጃህዲን ጋር የሶቭየት ድጋፍ የነበረውን የሀገሪቱ መንግስትን ለመጣል ሰርተዋል። ለዚህም ድጋፍ ለማግኘት ወደ አሜሪካ ተጉዘዋል።

ከሀገሪቱ የሶቭየት ድጋፍ የነበረው የናጂቡላህ መንግስት በ1984 ዓ.ም. ሲወድቅ ሙጃድዲን የትብብር መንግስትን በሀግሪቱ መስርቷል። ያኔ ካርዛይ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነውም ነበር። ከሁለት ዓመታት በኋላ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።

በሙጃህዲን ውስጥም ቢሆን የስልጣን ሽኩቻ አልጠፋም። ከዚያ በኋላም ወግ አጥባቂ የሚባለው ታሊባን በሀገሪቱ ስልጣን ተቆናጧል። መጀመሪያ ላይ ታሊባንን ቢደግፉም ኋላ በመቃወማቸው ካርዛይ ወደ ፓኪስታን በግዞት ሄደዋል። በ1991 ዓ.ም. ካርዛይ አባታቸው ተገድለዋል።

ለዚህም ታሊባን ጥፋተኛ ተደርጓል። ከሴፕቴምበር 11ዱ የአሜሪካ ጥቃት በኋላ ግን አፍጋኒስታን ላይ ዩኤስ እና ሌላው የዓለም ማህበረሰብ ባወረደው ውርጅብኝ ከስልጣን ሲወገድ ካርዛይ ይሄንን የአሜሪካን ተልዕኮ ለመደገፍ ከፓኪስታን ተመልሰዋል።

ከታሊባን ውድቀት በኋላ የሀገሪቱ የሽግግር መንግስት ሊቀመንበር ተደርገው ታስበዋል። የሀገሪቱ ሸንጎም ቢሆን የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንቱ እንዲሆኑ መርጧቸዋል።

ከታሊባን መውደቅ በኋላ የሀገሪቱን ተሰሚ መሪዎችን መቆጣጠሩ ብሎም ሁከትን ማስቆሙ ቀዳሚ ፈተናቸው ነበር። በሀገሪቱ የግድያ ሙከራዎች ኢላማም ነበሩ።

ይሁንና ግን ሀገሪቱ በ1987 ዓ.ም. አዲስ ህገ መንግስት ካጸደቀች በኋላ የሀገሪቱ የመጀመሪያው በህዝብ ተመራጭ ፕሬዝዳንት መሆን ችለዋል። ወደ ስልጣን ላይ ከመጡ በኋላ የምዕራባውያንን ድጋፍ ባያጡም፣ በሀገሪቱ የተረጋጋ ተቋም መፍጠር ግን ፈተና ሆኗቸዋል። በሙስናም ቢሆን በስልጣን ዘመናቸው መተቸታቸው አልቀረም።

መጀመሪያ ላይ የምዕራባውያኑ ድጋፍ የነበራቸው ካርዛይ ኋላም የዩኤስን በሀገሪቱ ያላትን ተሳትፎ መቃወም ጀምረዋል። በ2001 ዓ.ም. በአፍጋኒስታን 150,000 ያክል የውጭ ወታደሮች መኖራቸውን ተቃውመዋል።

የአሜሪካ ወታደሮች የአፍጋን ሲቪሎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚልም መረር ያለ ትችት ማቅረባቸው አልቀረም። የአሜሪካ ወታደሮች በሀግሪቱ እንዲቆዩ የሚፈቅድ የደህንነት ስምምነትን ከአሜሪካ ማድረግን እምቢ ብለዋል።

ሁለት ጊዜ ተመርጠው አፍጋኒስታንን በፕሬዝዳንት ያገለገሉት ካርዛይ ከፕሬዝዳንትነታቸው ማብቃት በኋላም ቢሆን በአፍጋኒስታን አሜሪካ ያላትን ጣልቃ ገብነት መተቸታቸው አልቀረም። የአፍጋን ማዕከላዊ መንግስት ከአሜሪካ ወታደሮች ጋር ያለውን ህብረትንም መተቸታቸው አልቀረም።

ታሊባን የአሜሪካን ወታደሮች እንዲያፈገፍጉ አድርጎ በቅርብ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረም በኋላም የሀገሪቱ መሪ ከሀገሪቱ ሲሸሹ፣ መንግስትን ወክለው ከታሊባን ጋር በአፍጋኒስታን የወደፊት ላይ በመደራደሩ ሀሚድ ካርዛይ ትልቅ ሚና ነበራቸው።

በአብርሃም በለጠ
2022-12-07