የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለፍርድ ቤቶች በተገቢው እየቀረቡ አለመሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለፍርድ ቤቶች በአግባቡ ለማቅረብ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ የሲቪል ተቋማትን እና ባለሙያዎችን አቅም ማጠንከር እንደሚገባም ተጠቁሟል።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት በሰላም ስምምነት ብንቋጭም አሁንም ቢሆን በተለያዩ የሀገራችን ክፍል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈጸሙ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ቀንን አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ወደፍርድ ቤቶች በማቅረብ በኩል ድክመቶች አሉብን ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለፍርድ ቤቶች ለማቅረብ እንደሃገር ያለን ልምድ ውስን መሆን እና የባለሙያዎች አቅም ውስንነት በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ መጠነ ሰፊ መሆን ተግዳሮት መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ማህበር ለሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክተር አቶ አማሃ መኮንን ነግረውናል። አቶ አማሃ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አቶ ሰለሞን የፌደራል እና የክልል የመንግስት አካላት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን የማክበር እና የማስከበር ሃላፊነቶች ቢኖሩባቸውም፣ ይህንን ሃላፊነታቸውን በመወጣት በኩል ክፍተቶች አሉባቸው ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን ለፍርድ ቤቶች ለማቅረብም በዘርፉ ላይ የሚሰሩ የሲቪል ተቋማትን ማበረታታት እንደሚገባ አቶ አማሃ ጠቁመዋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-12-08
