ሀገሬ ቲቪ

መፈንቅለ መንግስት በጀርመን

አውሮፓዊቷ ሀገር ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ እስካሁን የምትመራበት ዴሞክራሲያዊው ፌደራል ሪፐብሊክ መንግሥት ባንተ መመራት አምፈልግም የሚል የተደራጀ ተቀናቃኝ ቡድን ገጥሞታል።

ሀገሪቱ ለረጅም አመታት የምትመራበት ፓርቲ ከታጠቁ ቡድኖች የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጎበታል።

ገዢውን ፓርቲ አንቀበልም በማለት የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ ታጥቀው የተነሱት ቡድኖች የአንድ መጠነ ሰፊ የቀኝ ክንፍ ንቅናቄ አካል መሆናቸውን የጀርመን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የጀርመን ፖሊስ ይህን የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግስት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማውሉን ያስታወቀ ሲሆን በአስራ አንድ የጀርመን ግዛቶች ባካሄደው ምርመራ ንብረትነቱ የ52 ተጠርጣሪዎች ናቸው ያላቸውን 130 የሽብር እቃዎችን ማግኘቱን ገልጿል ።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት 25 ግለሰቦች ውስጥ 23ቱ ከ ሀገሪቱ 11 ግዛቶች ውስጥ የተገኙ ሲሆን ሁለቱ ዜጎች ደግሞ በ ኦስትሪያና ጣሊያን እንዲያዙ መደረጉን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል ።

ቡድኑ መፈንቅለ መንግስቱን ከፈጸመ በኋላ ሀገሪቱን እንዴት መምራት እንዳለበት ያወጣው ሰነድ መገኘቱንም የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል ።

ሄንሪች የተባለ ግለሰብ የዚህ መፈንቅለ መንግስት ዋና አቀናባሪ በመባል የተወነጀለ ሲሆን የቀድሞ የጀርመን የጦር አባላትም በሴራው እንደተሳተፉ እና ድርጊቱ በዋነኝነት ሲመሩት እንደነበር ተገልጿል ።

አቃቢ ህግ በቁጥጥር ስር የዋሉት ወንጀለኞች ባለፈው ዓመት በጀርመን የነበረውን የመንግስት ስርዓት ሽሮ በራሱ የመንግስት ስርዓት የመተካት አላማ ያለው አሸባሪ ድርጅት አቋቁሞ እንደነበር የገለጸ ሲሆን ይህን አላማቸውን ለማሳካት ወታደራዊ መንገድ መጠቀምን እንደመረጡና የጀርመን ፌደራል ፓርላማን በታጠቁ ቡድን አባላት ለማውደም በተለያዩ ጊዚያት ሙከራ ያደርጉ እንደነበር አስታውቋል ።

ተጠርጣሪዎቹ ሙሉ ለሙሉ አልተያዙም ያለው የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስተር አሁንም በጀርመን ሽብር ለመፈጸም እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅደው የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውንም ተናግሯል።

በዮሴፍ ከበደ
2022-12-08