የአበባ ልማት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በየአመቱ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሬ ለሃገሪቱ ብናስገባም የሃይል መቆራረጥ ለስራችን ተግዳሮት ሆኖብናል ብለዋል። ያመጣነውን የውጭ ምንዛሬ መልሰን ለነዳጅ ግዥ እያዋልነው ነው ብለዋል።
ኢትዮጲያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው እና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ዘርፎች ከቡና በመቀጠል የአበባ ልማት ዘርፉ በሁለተኛ ደረጃ ይጠቀሳል።
ባለፉት አምስት አመታት ያለውን እንኳ ብንመለከት በ2010 218 ሚሊየን ዶላር ሲያስገባ ይህ መጠን በ2014 470 ሚሊይን ዶላር ደርሶ እናየዋለን ። ከአበባው በተጨማሪ የአትክልትና ፍራፍሬው ሲጨመር ዘርፍ ባመት ከግማሽ ቢሊይን ዶላር በላይ ማስገኘት ላይ መደረሱን ልብ ይሉዋል።
ታዲያ ይህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በሚያመጣው የአበባ ዘርፍ ገበያው የሚፈልገውን ያህል በፍጥነት እንዳይጓዝ ብዙ ማነቆ የሆኑበት ጉዳዮች እንዳሉበት ይገለጻል።
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብትም በራሳችን አቅም ልንሰራቸው የምችላቸውን መሰረተ ልማቶች ማሟላት ብንችልም የሃይል መቆራረጥ በስራችን ላይ ተግዳሮት ሁኖብናል ይላሉ።
በአበባ ልማት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው ያሉት የአበባ አትክልና ፍራፍሬ አምርችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎደሮስ ዘውዴ ዘርፉ ያሉበት ተግዳሮቶች ቢኖሩም መንግስት ለዘርፉ እያደረገልን ያለው ድጋፍና ማበረታቻ ግን በበጎ ጎን የሚወሰድ ነው ብለዋል።
በአበባ እና አተክልትና ፍራፍሬ ዘርፉ የተስተዋሉ ተግዳሮችን መንግስት እና ባለሃብቱ ተቀራርቦ በመስራት ያሉትን እክሎች በመፍታት ዘርፉን አሁን ካለበት ደረጃ ማሳደግ እንደሚቻል ተገልጿል።
በማህሌት አማረ
2022-12-09
