ሀገሬ ቲቪ

የቻይና እና ሳውዲ ‘’አዲስ ምዕራፍ’’

ቻይና እና ሳውዲ አረቢያ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ወዳጅነታቸውን ለማጠንከር ተመካከሩ። ሀገራቱ ቻይና የምታስገባውን የሳውዲ ነዳጅ መጠን ለማሳደግም ተስማማተዋል። የቻይናው ዢ ወደ ሳውዲ ያደረጉትን ጉብኝት ለሀገራቱ አዲስ ምዕራፍ ነው ብለውታል።

ቻይና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለአረቡ ዓለም ብዙ ትኩረት አልሰጠችም የሚሉ ሀሳቦች ቀደም ብለው ይንጸባረቃሉ። ሳውዲ አረቢያ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ያላት ወዳጅነት መሻከር አሳይቷል።

በተለይም የኦፔክ አባል ሀገራት ሩስያን ጨምሮ የነዳጅ ምርታቸውን ለመቀነስ ሳውዲም መስማማቷን ተከትሎ የአሜሪካ ባለስልጣናት ከሳውዲ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንደገና ማጤን አለብን ሲሉ እንደነበር ይታወቃል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለሀገራቱ አዲስ ምዕራፍ ነው ያሉለትን የሳውዲ አረቢያ ጉብኝታቸውን አድርገዋል። ዢ ከሳውዲው መሪ ልዑል ሞሃመድ ቢን ሰልማን ተገናኝተው ስለሀገራቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት መክረዋል።

የዓለማችን ሁለተኛ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ቻይና እና በነዳጅ ሀብት የበለጸገችው ሳውዲ የስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነትንም አድርገዋል። ስምምነታቸው የቴክኖሎጂ ተቋሙ ህዋዌይን የሚመለከት ብሎም የሳውዲ ነዳጅ ወደ ቻይና በበለጠ መጠን እንዲገባም የሚፈቅድ ነው።

በርግጥ ግዙፏ የዓለማችን ነዳጅ አስገቢ ሃገሯ ቻይና በ10 ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ክፍያን ለሳውዲ ነዳጅ በያመቱ ታወጣለች አሁን ደግሞ ይሄው የነዳጅ ወዳጅነት እንዲያድግ ነው ስምምነታቸው።

የአረብ ሀገራት የአሜሪካ አለም አቀፋዊ ትኩረት መቀየርን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ማጤን ላይ ናቸው። በዩክሬይን ሩስያ ጦርነት የአሜሪካ እና አውሮፓውያኑ ትኩረት ሩስያን መቃወሙ ላይ ሲሆን የአረብ ሀገራቱ ከቻይና ወዳጅነትን የማጠንከር ፍላጎት ማሳየታቸው አልቀረም።

ከአረብ ሀገራቱ አንዷ ሳውዲ ደግሞ ወዳጅነቷን የማጠንከር ፍላጎቷን በግልጽ የቻይናውን ዢ ጂንፒንግን ተቀብላ ስምምነት በማድረግ አሳይታለች።

የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያም የሳውዲው ልዑል እጃቸው አለበት የሚሉት የምዕራባውያኑ ውግዘትም የሳውዲን ልብ ከአሜሪካ አርቆታል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ በሌላ በኩል ይሄው ክስተት ቻይና እንደተመራጭ አጋር በሳውዲ ዓይን እንድትታይ መሰረት ጥሏል የሚሉ አልጠፉም።

በአረቡ ዓለም የቻይና የግንባታ ተቋማት በተለይም በዱባይ እየሰሩ ይገኛሉ። ሳውዲ እና ቻይና የነዳጅ ግብይታቸውን ለማጠንከር ከመስማማታቸው በተጨማሪ የልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን የ500 ቢሊዮን ዶላር ኒወም የተሰኘ እጅግ የዘመነ ከተማ የመገንባት ዕቅድ ላይ የቻይና የግንባታ ተቋማት የመሳተፍ ዕድል ይኖራቸዋል።

ዢ ወደ ሳውዲ ያደረጉት ጉብኝት የሀገራቱን ወዳጅነት ይበልጥ ያጠነክራል የተባለለት ሲሆን፣ በጉብኝታቸው በቻይና የአረብ ሀገራት ውይይትም ላይ ይታደማሉ።

በአብርሃም በለጠ
2022-12-09