በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል ነው። ከግጭትና አለመረጋጋት ጋር በእጅጉ ይቆራኛል።ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና የዴሞክራሲ ተቋማትን እና የህግ የበላይነትን የሚያዳክም ነው። ሙስና። ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጸረ-ሙስና ቀን ተከብሮ ውሏል።
የቀኑ መከበር ዋንኛ ዓላማ ይህን ሀገራት እንዳያድጉ እንዳይለውጡ ትልቅ ሳንካ የኾነውን በሽታ ማስወገድ የሁሉም ሚና መኾንኑ ለማስገዝነብ፤ ስለሚያደርሰው ጉዳት ማሳወቅ እንደኾነ ቀኑን አስመልክቶ የተጻፉ መረጃዎች ያሳያሉ።
የዘንድሮ ዓለም አቀፍ ፀረ-ሙስና ቀን ሙስናን በመዋጋቱ እና እና በሀገር ደህንነት እንዲሁም ልማት መካከል ያለውን ወሳኝ ግንኙነት ማጉላትን ግቡ አድርጓል።
የዓለም ኢኮኖሚ በየዓመቱ 3.6 ትሪሊዮን ዶላር በሙስና ምክንያት እንደሚመዘበርበት የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ይህ ገንዘብ መሠረተ ልማት ለመገንባት፣ ሀገር የሚያስፈልጋትን ነገር ለሟሟላት ቢውል ምንያህል ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ማሰቡ ቀላል ነው። በተመሳሳይ በአውሮፓ ኀብረት አባል ከኾኑ ሀገራት በየዓመቱ 132 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በሙስና ምክንያት ይጠፋል።
በ2017 የተሠራ አንድ ጥናት ካካተታቸው 25% የሚኾኑ ተሳታፊዎች እጅ መንሻ አሊያም ጉቦ ሳንሰጥ ሕዝባዊ አገልግሎቶችን ማስፈጸም አልቻልንም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሀገራት በዘላቂ የልማት ሥራዎቻቸው ላይ ማሳካት የሚፈልጉት ግቦች እንዲሟሉ ከተፈለገ ሙስናን መከላከል፣ ግልፅነትን ማስፋፋትና ተቋማትን ማጠናከር ወሳኝ ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ላይ የጻፈው መልዕክት ያሳያል።
የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሰራተኞች፣ የህግ አስከባሪዎች፣ ብዙኃን መገናኛዎች ፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የትምህርት ተቋማት፣ በአጠቃላይ ሁሉም ሕዝብ ሙስናን በመዋጋቱ ረገድ ሁሉም ሚና አላቸው።
ኢትዮጵያም ይህን ለለውጥ እና ለዕድገት ጸር ኾኖ አላንቀሳቅስ ብሎኛል ያለችውን ሙስና ለመዋጋት ቆርጣ መነሳቷን አስታውቃለች። የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እና ግለሰቦች ላይም ጥብቅ ምርመራ እንደተጀመረ ይታወቃል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-12-09
