መቼም ፍልሰት የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው። ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላው ቦታ መጓዝን የሰው ልጅ በተፈጥሮው ይማረዋል።
ይህንን ያልናችሁ ያለምክኛት አይደለም ከወደ ስፔን የሰማነው ዜና ቀልባችንን ያዝ ቢያደርገው እንጂ።
228 ተሳፋሪዎችን ያሳፈረው ኤርባስ A321 አውሮፕላን ከሞሮኮ ካዛብላንካ የተነሳው ተርኪየ ኢስታምቡል ለመድረስ በማለም ነበር።
ታዲያ በጉዞው መሀል አንዲት ሴት ልወልድ ነው የሽንት ውሃ ፈሶኛል ማለት ትጀምራለች። አብራሪዎቹም የሰው ልጅ ክቡር ነው እና ወዲያውኑ መዳረሻቸውን መቀየር ነበረባቸው። የጉዞ አቅጣጫቸውን ቀይረው መዳረሻቸውን ስፔን ባርሴሎና አደረጉ።
ነገሩ ታዲያ እዚ ጋር ነው የተፈጠረው። አውሮፕላኑ ለድንገተኛ እርዳታ ፍለጋ በቆመባቸው ሰዓታት ውስጥ በአውሮፕላኑ የነበሩ ስደተኞች ወርደው ሮጠው አምልጠዋል።
የስፔን መንግስት እንዳለው ከሆነ 28 የሚሆኑት ስደተኞች ከአውሮፕላኑ አምልጠዋል። 14ቱ ወዲያውኑ በአየር ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ሲውሉ፤ 2 ደግሞ በፍለጋ ተገኝተው ሊያዙ ችለዋል።
ልወልድ ነው ያለችዋ ሴትም በምርመራ ነብሰጡር አለመሆኗን ማረጋገጣቸውን የስፔን ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሮይተርስ አስነብቧል። ፖሊስ ነብሰጡር ነኝ ያለችዋን ሴት በቁጥጥር ስር አውሏታል።
በፖሊስ ከተያዙት ውስጥ 5ቱ ወዲያውኑ ወደ ተርኪዬ ወደሚሄደው አውሮፕላን ሲጫኑ 8 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ሞሮኮ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ዘገባው አትቷል።
አምልጠዋል ካላቸው 28 ተሳፋሪዎች ውስጥ 12ቱን ፖሊስ አሁንም ሊያገኛቸው እንዳልቻለም ፖሊስ አስታውቋል።
የስፔን ፖሊስ ከሁለት ወራት በፊትም እንዲሁ በአየር ማረፊያ ውስጥ ከአውሮፕላን ወርደው ካመለጡ 24 ተሳፋሪዎች ውስጥ 12ቱን ብቻ በቁጥጥር ስር አውሎ ነበር። ያኔም 12 ሰዎች የገቡበት ሳይታወቅ ቀርቷል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-12-09
