ድንበር ሀገርን ከሀገር ይለያል፤ የድንበር ተገፋብኝ ቅሬታዎች ደግሞ ብዙ ሀገራትን አጋጭተዋል ንጹሀንን ለስደት ዳርገዋል ።
ታዲያ ድንበሬን ነካህ በሚል የሚቀሰቀስ ግጭት ብዙ ሀገራትን ደም በሚያፋስሱበት በዚህ ዘመን በሁለት ሀገራት ስለምትመራ አንዲት ደሴት መኖሯን ሰማንና ልናጋራቹ ወደድን ።
ፊዛንት ትባላለች በስፔንና በፈረንሳይ ድንበር ላይ የምትገኝ አስገራሚ ታሪክን የያዘች አነስተኛ ደሴት ናት ። አንድ ቋሚ ሀገር የሌላት ይቺ ደሴት ለ 6 ወር የስፔን ስድስት ወሯን እንደጨረሰች ደግሞ ንብረትነቷ የፈረንሳይ በመሆን ታገለግላለች።
ታዲያ አንድን ቦታ ሁለት ሀገራት በጊዜ ገደብ መምራት ባልተለመደባት ዓለማችን የዚች ደሴት በሁለት ሀገር መመራት ብዙዎችን ያስገርማል ። ነገሩ እንዲ ነው ። ከ 100 አመታት በፊት በስፔንና በፈረንሳይ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ጦርነት ይቀሰቀሳል።
ይህ በጊዜ ስምምነት ላይ ሊደርስ ያልቻለው ግጭት ብዙዎችን እየቀጠፈ ረጅም አመታትን አስቆጠረ ። መንግስቶች ቢለዋወጡ ለድርድር የተለያዩ መድረኮች ቢዘጋጁም በሁለቱ ሀገሮች መካከል አልሸነፍ ባይነት ነገሰ።
ታዲያ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከ 3 አስርት አመታት በኋላ ግጭቱ ያበቃ ዘንድ ሁለቱ ሀገሮች ከፍተኛ ባለስልጣናቶቻቸውን ወደዚች ደሴት ለድርድር ላኩ ። በወቅቱ ስምምነት ላይ ባይደርስም ደሴቷ ድርድሩን ማኪያሄድ ከጀመረች ከ11 ዓመታት ከ24 የመሪዎች ውይይት በኋላ ይህ ብዙ ህዝብን የፈጀው ጦርነት ከስምምነት ደረሰ።
ደሴቷ ይህን ታሪካዊ ስምምነት ከማድረግ ባለፈ የወቅቱን የፈረንሳዩ ንጉሥ ሉውስ አሥራ አራተኛን ልጅ ከስፔኑ ንጉሥ ሴት ልጅ ጋር ድል አድርጋ ዳረች ።
የሁለቱ ሀገራት መነቋቆር እስከወዲያኛው እንዲያበቃ ይቺ ደሴት በጋብቻ አዛመደች ። ይህን ታሪካዊ ስምምነት ምክንያት በማድረግ በዛው የጋብቻ ስነስርዐት ላይ ደሴቷ በሁለቱ ሀገራት በግዜ ገደብ እንድትመራ ውሳኔ ተላለፈ ።
ከ100 ዓመታት በፊት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ቢቀያየሩም ፊዛንት ደሴት ቃል በተገባው መሰረት 6 ወር የ ስፔን 6 ወር የፈረንሳይ በመሆን ያለ አድሎ እያገለገለች ትገኛች ።
ድንበር ለብዙ ሀገራት ግጭት መንስኤ በሆነበት ዘመን አሁን ተራው ያንቺ ነው በማለት በፍቅር የሚመሯት ሁለቱ ሀገራት ለብዙዎች ማስተማሪያ ናቸው።
በዮሴፍ ከበደ
2022-12-12
