በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ የኾነው የተሁለደሬ ወረዳ ከመሬት ሌብነት ጋር በተያያዘ ሰፊ ችግር የሚስተዋልበት እንደኾነ ይነገራል።
በዞኑ ከመሬት ሌብነት ጋር በተያያዘ በሁሉም ወረዳዎች የህዝብ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ተካሔዷል። በዚህ መድረክ የይዞታ ደብተር ለማግኘት እስከ 20 ሺብር ገንዘብ እንደሚጠየቁ እና በሕገወጥ መንገድ ይዞታቸው እንደተነጠቁ አርሶአደሮች ተናግረዋል።
የተወሰኑ አርሶአደሮች ጉቦ ሰጥተው የይዞታ ደብተር ያላገኙና ሐሰተኛ የሆነ ነጭ ወረቀት የተሰጡም እንዳሉም ነው የገለፁት፡፡ ከዚያ ባሻገር ይህን እንዲያደረጉ ያስገደዷቸውን የባለሙያዎቹን ስም በመጥቀስ ጭምር የደረሰባቸውን በደል አብራርተዋል።
የተሁለደሬ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ መቅደስ እብሬ በወረዳው መሬት ጽ/ቤት ከ900 በላይ የሚሆኑ ሕገ-ወጥ የገጠር መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተሮች ተቆልፈው መገኘታቸውን አስታውቀዋል።
ይህ የሌብነት ሰንሰለት ከታች ከአርሶአደሩ ጀምሮ የተሳሰረ እንደኾነ ገልጸው በዚህ ሌብነት ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎችም በሕ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ይህን የገነገነ ሌብነት ለመከላከልና የመሬት ሌቦችን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ አሁንም እየተሰራ እንደኾነ ጠቁመው አርሶ አደሩ ሥጋት እንዳይገባው እና ከጎናቸው እንዲኾን ጠይቀዋል። መረጃውን የደቡብ ወሎ ዞን መንግሥት ኮምኒኬሽን ነው የላከልን።
በሙሉጌታ በላይ
2022-12-12
