ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለምድራችን ከፍተኛ ራስ ምታት የሆነውን የአየር ንብረት ብክለትን ለመታገል ብዙዎች በተለያዩ መድረኮች ድምጻቸውን ያሰማሉ ።
አየር ንብረትን ከሚበክሉ ተግባራት እንድንቆጠብ የተማጽኖ መልዕክት ከሚያሰሙት መካከል የ16 ዓመቷ ታዳጊ ግሬታ ቱንበርግ አንዷ ናት ። አንዳንዶች የ አየር ንብረት ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ እንኳን በቅጡ በማይረዱበት እድሜ የ 16 ዓመቷ ታዳጊ ይህን ማድረጓ ከአለም አድናቆት ተችሯታል።
ታይም መጽሄትም በየዐመቱ ድንቅ ስራ የሰሩ ታላላቅ ሰወችን ክብር በሚሰጥበት ዝግጅቱ ይቺን ታዳጊ ከ 3 ዓመት በፊት በዛሬዋ ቀን የ ዓመቱ ተጽኖ ፈጣሪ ሰው ሲል ክብር ሰጥቷል።
በብዛት በዕድሜ ገዘፍ ያሉ እና ለምድራቸው በጎ ነገርን ያበረከቱ ሰወች የሚያገኙትን ክብር ግሬታ ገና በ16 ዓመቷ በማግኘቷ በ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተወልዳ የዓመቱ ተጽኖ ፈጣሪ ሰውን ክብር የተቀበለች የመጀመሪያዋ ታዳጊም አድርጓታል ።
ቤተሰቦቿ የሚያደርጉትን አየር ንብረት ጎጂ ተግባራትን በመቃውም መቆርቆር የጀምረችው ታዳጊዋ በትምህርት ቤቶች እና በአካባቢዋ ምድራችንን እናድን ስትል ምድር ምን ያህል እንደታመምች ለማስረዳት ትሞክራለች ።
ይህን መልዕክቷን ለመላው አለም ማስተላለፍ ፍላጎት እንዳላት የተረዱት ቤተሰቦቿ በመቻቹላት እድል በስዊድንና በመላው የአውሮፓ አገሮች በመዟዟር
“ምድራችን በእሳት እየነደደች ነው ፤ አለም ሚያስጨንቃት ገንዘብና የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻ ነው ፤ በጅምላ መጥፋት ጀምረናል እባካቹ እንድረስላት” ስትል የተማጽኖ ድምጿን ማሰማት ጀመረች ።
በመድረኩ የተገኙ ሁሉ ይህ ንግግር ከዚች ታዳጊ አንደበት በመውጣቱ ልባቸው ይነካል በሚችሉት ሁሉ ምድራቸውን ለማዳን እንደሚረባረቡም ቃል ይገባሉ። ቱንበርግ ከአውሮፓ አልፋ በአሜሪካና በተለያዩ ሀገራት በተዘጋጁ ታላላቅመድረኮች ላይ በመገኘት የምድርን ህመም አስረድታለች ።
ምንም እንኳን የ አየር ንብረት መበከል አሁንም የምድራችን ፈተና ቢሆንም ይቺ ታዳጊ የጀመረቻቸው እንቅስቃሴዎች ስለችግሩ ብዙዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ቀላል የማይባል ሚና ተጫውቷል ።
ለዛም ነው በ2019 በዛሬዋ ቀን የ16 አመቷ ታዳጊ የአመቱ ተጽኖ ፈጣሪ ሰው የሚል ክብር የተሰጣት ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-12-13
