ሀገሬ ቲቪ

የህግ ባለሙያዎች የመብት ጥሰቶችን በህብረት ለመሞገት

በሀገራችን የመብት ጥሰቶችን የህግ ባለሙያዎች በህብረት የመሞገት ልማዳቸው ደካማ መሆኑ ተገለጸ። የምስራቅ አፍሪካ የህግ ባለሙያዎች በሰብዓዊ መብቶች ላይ ምክክር አካሂደዋል።

በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ለሰብዓዊ መብቶች ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የህግ ባለሙያዎችን አካቶ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ምክክር አካሂዷል።

ከተመሰረተ ሶስት ዓመት የተጠጋው የማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማኃ መኮንን የሀገራችን የመንግስት ስርዓቶች የመብት ጥሰቶች የሰፈኑባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አቶ አማኃ በዜጎች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የህግ ባለሙያዎች በህብረት የመሞገት ልማዳችንም ደካማ ነበር ብለዋል። የመብት ጥሰቶችን የህግ ባለሙያዎች በህብረት የሚሞግቱበትን ባህል ለመፍጠር እየሰራን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሰብዐዊ መብት ኮሚሽን የሴቶች እና ህጻናት መብቶች ኮሚሺነር መስከረም ገስጥ የህግ ባለሙያዎች በጋራ የሚያደርጓቸው ምክክሮች አቅማቸው እንዲጎለብት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የህግ ባለሙያዎች የጋራ ምክክር ማድረጋቸው ሙያዊ ህብረት እና የልምምድ ልውውጥ እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሏል።

በአብርሃም በለጠ
2022-12-13