ሀገሬ ቲቪ

146 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ገቡ

መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ የያዙ 146 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ገብተዋል አለ። ወደ ክልሉ ከሄዱት መካከል ዘጠኙ የነዳጅ ቦቴዎች መሆናቸውም ተሰምቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንቱ የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የማቆም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ወደ ትግራይ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ያለገደብ እየገቡ ነው ብለዋል። የተፈለገውን ያህል ድጋፍ የሚያደርግ የተራድኦ ድርጅት አለመኖርና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሽባሪነተ የተፈረጀው የሕውሃት ቡድን አሁንም በአፋርና በአማራ ክልል አንዳንድ ወረዳዎችን በወረራ መያዙ የሰብዓዊ ድጋፉ ያን ያህል እንዳይሳካ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በሌላ በኩል በሶማሌ፣ ኦሮሚያና አፋር ክልሎች የዝናብ እጥረትን ተከትሎ በተከሰተው የምግብ እጥረት ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ዜጎች እንዲኖሩ በማድረጉ የእርዳታ እጥረት እንደሚያጋጥም ተገልጿል። በሳኡዱ አረቢያ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር በመመለሱ ሂደት እስካሁን 15 ሺሕ 300 ኢትዮጵያን መመለሳቸውም በመግለጫው ተነስቷል።

በሀገሬ ቲቪ
2022-04-29