ለሸገር አዲስ ገጽታ ፕሮጀክት በከተማዋ በተመረጡ ቦታዎች የሚገኙ የፌደራል መሥሪያ ቤት ይዞታዎች በተሻለ መልኩ መልማት እና ገቢ ማስገኘት የሚችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ፕሮጀክት ነው።
ለነዚህ ይዞታዎች የተለየ እና ውብ የኾነ ዲዛይን ለውድድር ቀርበው ሕዝብ እንዲመለከታቸው አስተያየቱን እንዲሰጥባቸው ተደርጓል።
ሀገሬ ቴሌቭዥንም ከዲዛይን ውድድሩ በኋላ ምን አዲስ ነገር አለ፤ ለውድድር ከቀረቡ ዲዛይኖችስ አሸናፊ የኾነው ተለየ ሲል የፌደራል የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽንን ጠይቋል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር የኾኑት ሌንሳ መኮንን፡ ዲዛይኖቹ አሁንም በግምገማ ላይ እንደኾኑ ነግረውናል።
በዚህ ፕሮጀክት ከቦሌ አየር ማረፊያ እስጢፋኖስ አራትኪሎ እስከ አሜሪካ ኤምባሲ እንዲሁም ከቦሌ አየር ማረፊያ፣ መስቀል አደባባይ፣ ስታዲየም ቸርችል ማዘጋጃ ቤት ባሉ ሁለት መስመሮች የሚገኙ የፌደራል መስሪያ ቤት ይዞታዎችን ገቢ ወደሚያስገኝ ዲዛይን ለመለወጥ ታቅዷል።
አሸናፊው ዲዛይን ከታወቀ ፕሮጀክቶቹ በግል አልሚዎች ይልሙ ወይስ በመንግሥት እንዴት ባለ ሁኔታ ግ ንባታዎቹ ይከናወኑ በምን ያህል ጊዜ ውስጥስ መፈጸም አለበት የሚለው ቀጣይ ሥራ ነው ተብሏል።
አሁን በዲዛይን ላይ ካለው ፕሮጀክት በተጨማሪ ከቦሌ አየር ማረፊያ መገናኛ ባለው መንገድ የሚገኝ የፌደራል መ/ቤት ይዞታዎችን የማልማት ሥራ በዕቅድ ተይዟል ከዚያ ባሻገር በተለያዩ ክልሎችም መሰል ሥራዎች ይቀጥላሉ።
ይህ ፕሮጀክት የሥነ ህንፃ ፣የአካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች ባለሙያዎች በጋራ አሳታፊ የሚያደርግ እንደኾነ ነው የተነገረው።በቀጣይ ፕሮጀክቱ በሚካናውንበት እና በተጠቀሱት መዳረሻዎች የሚገኙ የፌደራል መስሪያ ቤቶች በሌላ አካባቢ ሰብሰብ ብለው አገልግሎት የሚሰጡበት እና የሚገነቡበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ሰምተናል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-12-14
