የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ በኢራቅ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ አንድ ጋዜጠኛ ጫማውን ወርውሮባቸው ነበር። የኢራቁ ጋዜጠኛ ፕሬዝዳንቱ ላይ ይህንን ድርጊት የፈጸመው በዛሬዋ ዕለት በ2001 ዓ.ም. ነበር።
በጊዜው አሜሪካ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ለመፈለግ በሚል ዘመቻን በኢራቅ ላይ ከጀመረች ስድስት ዓመታት አልፈው ነበር።
ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች አሏት በሚል ወታደራዊ ዘመቻዋን በሀገሪቱ ላይ ከጀመረች ስድስት ዓመታት አልፈዋል።
በጊዜው በ2001 ዓ.ም. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ደግሞ የስልጣን ወንበራቸውን ከመልቀቃቸው አስቀድሞ ለመጨረሻ ጊዜ ኢራቅን ለመጎብኘት ተጉዘዋል።
በባግዳድ ከኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኑሪ አል ማሊኪ ጋር የተገናኙት ቡሽ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡም ነበር። ጆርጅ ቡሽ በመግለጫው ኢራቅን የደበደብነው ለዓለም ሰላም አስፈላጊ ስለነበር ነው ብለው መከራከራቸው አልቀረም።
የ28 ዓመቱ ኢራቃዊ ጋዜጠኛ ሙንታዳር አል ዛይዲ በቡሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ታድሟል። ይሄው ጋዜጠኛ በግብጽ ላለው አል ባግዳድያ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሰራ ነበር።
ለወጣቱ ኢራቃዊ ጋዜጠኛው ለስድስት ዓመታት በአሜሪካ ዘመቻ የተጎሳቆለችው ኢራቅን የማጥቃታቸውን አስፈላጊነት ለዓለም ሰላም ነው ብለው ጆርጅ ቡሽ መግለጻቸው አላስደሰተውም። አስቆጥቶታልም።
ዛይዲ ወደ ቡሽ ጫማውን ወረወረ። “ይህ ከኢራቃውያን ለርስዎ፣ የስንብት የመሳም ስጦታ ነው” ሲልም በአረቢኛ ቁጣውን አከለበት።
ዛይዲ ሁለቱንም ጫማዎቹን ወደፕሬዝዳንቱ ከመውረወሩ በተጨማሪ ይሄ ከመበለቶች፣ ወላጅ አልባዎች እና በኢራቅ ከተገደሉት የተላከ ነው ሲልም አከለበት። በዚያ የነበሩት ጠባቂዎች ዛይዲን ይዘው ከመግለጫ ክፍሉ አስወጡት ወደ እስር ቤትም ወሰዱት።
ጆርጅ ቡሽ ያልተጠበቀውን ክስተት ተከትሎ በመቀለድ አልፈዉት ጥያቄ መቀበላቸውን ቢቀጥሉም፤ ለሪፖርተሮቹ ይሄንን የአንድ ሰው የጫማ መወርወር ክስተት የሙሉ ኢራቅ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አድርጋችሁ ልትወስዱት ትችላላችሁ ብዬ አላስብም ብለዋል።
የኢራቅ መንግስት የዛይዲን ድርጊት ቢኮንንም ወጣቱ ጋዜጠኛ ግን በአረቡ ዓለም እንደጀግና መቆጠሩ አልቀረም። የዳዊት እና ጎልያድ ምሳሌ ተደርጎ መቅረቡም አልቀረ።
የዛይዲ ድርጊት ከአስር ዓመታት በኋላም ቢሆን በቡሽ የፕሬዝደንትነት ዘመን የሚታወስ ቪዲዮ ሆኗል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ከእስር እንዲፈታ ጠይቀውለታል። የልጃችንን እንድርልሃለን ቃል መግባቶችም ተዥጎድጉደውለታል።
የሳውዲ ባለሀብት ለታሪካዊው ጫማው 10 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ብሎም እንደነበር ተዘግቧል። የዛይዲ ቀጣሪ አለቃው እንደተፈታ የሚገባት ባለ አራት መኝታ እያስገነባለት መሆኑንም በጊዜው ገልጿል።
ወቀሳም ሙገሳም በድርጊቱ የጎረፉለት ዛይዲ የውጭ ሀገር ባለስልጣንን በመመታት ወንጀል ተፈርዶበት ከሶስት ዓመታት እስር በኋላ ሲፈታ በእስር ስቃይ እንደደረሰበት ገልጿል። ከኢራቅ ወጥቷልም።
የግል ተሞክሮውን “The Last Salute To President Bush” በሚል መጽሃፍ የጻፈ ሲሆን፣ ይሄው መጽሃፉ በሆሊውድ የፊልም አዘጋጅ ወደ ፊልም ተቀይሯል። ለኢራቅ ምክር ቤት ቢመረጥም ስኬታማ ግን አልሆነም።
በአብርሃም በለጠ
2022-12-14
