ሀገሬ ቲቪ

የተመድ ድጋፍ በትግራይ

የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) በፌደራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በአማራ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ አራት መተላለፊያዎች ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እየደረሰ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ቢሮው እንዳለው ከኅዳር 6 እስከ ኅዳር 29፣ ባሉት ቀናት በተመድ አጋሮች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከ1 ሺሕ 600 በላይ በሚሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ተልኳል።

ከ63 ሺሕ 800 ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ከ4 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የጤና፣ የመጠለያ፣ የትምህርት፣ የውሃ እና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ትግራይ መድረሳቸውንም መግለጫው አመልክቷል። ተደራሽነቱን ለማስፋት ተከታታይ ሰብዓዊ በረራዎች እየተካሄዱ መሆኑንም አስታውቋል።

በብሩክ ያሬድ
2022-12-16