ሀገሬ ቲቪ

የአውሮፓ ህብረት ዘጠነኛ ማዕቀቡን ሩስያ ላይ ጣለ

የአውሮፓ ህብረት በዘጠነኛው የሩስያ ላይ ማዕቀቡ በ200 ሩስያውያን ላይ ማዕቀብ ጣለ። ህብረቱ ለዩክሬይን ተጨማሪ 18 ቢሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምቷል።

ከተጀመረ 10 ወራትን ባስቆጠረው የሩስያ ዩክሬይን ጦርነት፣ ከዩክሬን ጎን የቆመው የአውሮፓ ህብረት ሩስያን ያዳክምልኛል ያለውን ማዕቀብ በሩስያ ላይ ለስምንት ጊዜያት ጥሏል። የጣላቸው ማዕቀቦች ግን ሩስያን ሳይሆን ራሱን የአውሮፓ አህጉርን የጎዱ ናቸው የሚል ትችትን ሲያስከትልበት ቆይቷል።

ባሁኑ ምክክሩ ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ በሀገሪቱ ላይ ማዕቀብን ጥሏል። የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በዚህኛው ጉባኤያቸው የ18 ቢሊዮን ፓውንድ ድጋፍን አሁንም ለዩክሬይን በቀጣዩ ዓመት ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በሩስያ ላይ የተጣለው አዲሱ ማዕቀብ ከ200 በላይ ግለሰቦችን ይነካል፤ እነዚህ ግለሰቦችንም እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በጥቁር መዝገብ ላይ እንዲሰፍሩ ያደርጋል የተባለለት ሲሆን፣ የሩስያ የማዕድን ዘርፍ ላይ ኢንቨስትመንትን እንዳይካሄድም የሚከለክል ስለመሆኑ ተጠቁሟል።

ዝርዝር መረጃ ህብረቱ ባያወጣለትም ይሄ የ2022 የመጨረሻ ጉባኤው በሆነው በዚሁ ጉባኤው የአውሮፓ ህብረት ሩስያ ላይ የዓመቱ የመጨረሻ ያለውን ይሄንንው ማዕቀቡን አሳልፏል።

ይሄንን ማዕቀብ የህብረቱ አባል ሀገራት በጋራ እንደሚያጸድቁትም ጥቆማዎች አሉ። ሁሉም እስኪያጸድቁትም የመጨረሻ ዝርዝሩን ከማቅረብ ህብረቱ ተቆጥቧል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሺን ባሳለፍነው ሳምንት 200 ሩስያውያንን ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ ብሎም የእንቅስቃሴ ገደብ እንደሚያደርግባቸው አስታውቆ ነበር።

ይሄው ማዕቀብ የመንግስት ባለስልጣናት ሚኒስትሮችን፣ ህግ አውጭዎችን፣ ወታደራዊ አዛዦችንም ጭምር ያካተተ ነው። እስካሁን ከ1200 በላይ ግለሰቦች ላይ ህብረቱ ከዩክሬይኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ማዕቀብ ጥሏል።

ይሄንን ማዕቀብ የግብርና ምርቶችን ወደውጭ በሚልኩ በሩስያ ባለሀብቶች ላይም መጣሉን የተቃወሙ የህብረቱ ሀገራትም አልታጡም።

የዓለም አቀፉን የምግብ ቀውስ ይበልጥ ላለመባባስ በተናጠል የሩስያ የግብርና እና የምግብ ምርቶች ንግድ ላይ ማዕቀብ ከመጣል ህብረቱ ተቆጥቧል። ሆኖም ማዕቀቡ ከሩስያ ባለሀበቶች ጋር አውሮፓውያኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዳይሰሩ የሚከለክል መሆኑ በዚሁ የሩስያ የግብርና ምርቶች የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም የሚሉም አልታጡም።

ቀደም ያሉት የህብረቱ ማዕቀቦች ሩስያን ከጦርነቱ ባያስቆሟትም በዚህኛው ማዕቀቡ ባንኮቿም የሀገሪቱ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ላይም ኢላማውን አድርጎ ፣ ሩስያን ለማዳከም ዩክሬይንን ደግሞ ለመደገፍ ዓልሞ ዘጠነኛ ማዕቀቡን ጥሏል።

በአብርሃም በለጠ
2022-12-16