ሀገሬ ቲቪ

የአፍሪካ የጤና ባለሞያዎችን በአንድ ጥላ ስር ያቀፈ ስርዐት ይፋ ሆነ

ሀገራችን የጤና ስርዐቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን ታማሚዎች ለበሽታቸው በቀላሉ መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራች ብትገኝም አሁንም ግን ሕክምናዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር አስተሳስሮ አገልግሎት መስጠት ላይ ብዙ መስራት ያስፈልጋል።

የጤና አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ማዘመንን አላማ አርጎ የተነሳው አፍሪካን ቴሌ ሜዲስን ኔትዎርክ የአፍሪካን የጤና ባለሞያዎች በዲጂታል መንገድ በአንድ ጥላ ስር አስተሳስሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።

የተቋሙ መስራች ዶ/ር አከዘ ጣዕመ የአፍሪካ ሀኪሞችን በአንድ ቋት ማስተሳሰሩ ታማሚዎች ከሀገራችን እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዶክተሮች ጋር የሚገናኙበት መንገድን ከመፍጠሩም በላይ የሀገራችንን የዲጂታል ሕክምና አሰጣጥ ለማዘመን የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

በተቋሙ የተካተቱ ዶክተሮችን ከ ታማሚዎች ጋር በቀላሉ ለማገናኘትም ሀባሪ ዶክ የተሰኘ መተግበሪያ በልፅጎ በበይነ መረብ አማካኝነት ባሉበት የጤና አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚችሉ ነግረውናል ።

የህክምና አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የ10 አመት ዕቅድ መነደፉን የጠቆሙት የጤና ሚኒስተር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ መሰረተ ልማቶችን የማስፉፉት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለህመማቸው መፍትሔ ለማግኘት መተግበሪያውን የሚጠቀሙ ሰወች የፈለጉትን ቋንቋ እና ሀኪም መርጠው መታከም እንደሚችሉ ተገልጿል።

በዮሴፍ ከበደ
2022-12-16