ሀገሬ ቲቪ

የውሃ አቅርቦት እና ፍላጎት ያልተመጣጠነባት አዲስ አበባ

በአዲስ አበባ የውሃ አቅርቦት እና ፍላጎት የተመጣጣነ አለመሆኑ ተገለጸ። ለዚህም ከተማዋ የፈረቃ ስርዓትን እየተከተለች ቢሆንም የመብራት ኃይል መቆራረጥ ፈረቃውን እያስተጓጎለው መሆኑም ተጠቁሟል።

አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ውሃ ለማዳረስ የፈረቃ ስርዓትን እየተከተለች ቢሆንም ተዛውውረን ያናገርናቸው አስተያየት ሰጭዎች ፈረቃውም ቢሆን እየተስተጓጎለ ነው ብለዋል።

ስለጉዳዩ ምላሽ የሰጡን የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሰርካለም ጌታቸው የከተማዋ የውሃ ፍላጎት እና አቅርቦት የተመጣጠነ አለመሆኑን ገልጸውልናል።

725 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በቀን ቢቀርብላትም 1.2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በቀን ያስፈልጋታል ያሉ ሲሆን ለዚህም የፈረቃ ስርዓትን እየተከተልን ነው ብለዋል።

ከተማዋ እየተከተለች ያለችውን የውሃ የፈረቃ ስርዓትንም የመብራት ኃይል መቆራረጥ ትልቁን ድርሻ ቢወስድም የፓምፕ መቃጠል እና ሌሎችም ቴክኒካዊ ችግሮች በማስተጓጎል ቅሬታ እየፈጠሩ መሆኑን ጠቁመውናል።

የከተማዋን የውሃ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን ለመፍታትም ተጨማሪ ጉድጓዶችን የመቆፈር ዕቅድ መያዙን ነግረውናል።

ውሃ እያላቸው የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ጉድጓዶች እየተቆፈሩ ሲሆን 570 ሚሊዮን ብር ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ነግረውናል።

በከተማዋ 18 ወረዳዎች በሳምንት አንዴ ብቻ ውሃ ያገኛሉ።

በአብርሃም በለጠ
2022-12-19