ሀገሬ ቲቪ

ጨዋታ ለመመልከት ባስ የጠለፈው ደጋፊ

ይህ ሰዐት በኳስ ፍቅር ለነደዱት ለማራዶና ሀገር ሰወች ከባድ የምጥ ሰዓት ነው። አርጀንቲና ከ ክሮሺያ የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ ሊጀምር ጥቂት ደቂቃዎች ቀርተውታል።

የሞላለት የሀገሩን ገድል ለመከታተል በኳታር ግዙፍ ስታዲየም ሲገኝ ያልሆነለት ደግሞ ቤቱ ባለው የቴሌቭዥን መስኮት አይኑን ተክሎ ድሉን ይጠባበቃል። ታዲያ እንደማንኛውም ሀገር ወዳድ አርጀንቲናዊ ጨዋታው ሊጀምር ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው ከስራ ቦታው የወጣ ግለሰብ ወደ ሰፈሩ በሚወስደው አውቶብስ ውስጥ ገብቶ ጉዞ ይጀምራል።

ነገር ግን ይህ የ 53 ዓመት ኳስ አፍቃሪ ግለሰብ እየተጓዘበት ባለው የህዝብ ትራንስፖርት ፍጥነት ተበሳጭቷል። እሱ በጊዜ ገብቶ የሀገሩን ጨዋታ መከታተል ቢፈልግም መሪ የጨበጠው ግለሰብ ግን በፈለገው ፍጥነት ሊነዳለት አልቻለም።

እባክህ በፍጥነት ንዳው ጨዋታው ሊያመልጠን ነው የሚል ተማጽኖ ቢያቀርብም ሹፌሩ ግን ጭራሽ መኪናውን አቁሞ ዕቃ ለመሸመት ወደ ሱቅ አመራ። ያን ጊዜ ጨዋታው ሊያመልጠው ያልፈለገው ይህ ግለሰብ አንድ ሀሳብ መጣለት።

የቆመውን መኪና ከነተሳፋሪው አስነስቶ ወደ ቤቱ መንዳት ። እንዳሰበውም አውቶብሱን ከነተሳፋሪዎቹ ይዞ በከፍተኛ ፍጥነት ወደቤቱ ነዳው ።

የኳስ ፍቅር እና የሀገር ፍቅር ተደማምረው የፈጠሩት አስገራሚ ውሳኔ። አውቶብሱ ያለማንም ከልካይነት 4 ኪሎሜትሮችን ቢነጉድም ከዋናው ሹፌር ጥቆማ በደረሳቸው ፖሊሶች አጋዥነት ካሰበበት ሳይደርስ መኪናውን ለማቆም ተገደደ።

የጓጓለትን ጨዋታ ለመከታተል መሰዋትነት ቢከፍልም መዳረሻው እንዳሰበው ቤቱ ሳይሆን እስር ቤት ሆነ። ፖሊስ አውቶብስ ጠልፎ በማምለጥ ክስ የመሰረተበት ሲሆን ይህ ግለሰብ ግን ይህን ሁሉ ዋጋ ከፍዬ ሀገሬ ብትሸነፍ ጸጸቱን አልችለውም ነበር ግና አርጀንቲና 3 ለ 0 በማሸነፏ ከዚህ በኋላ በእስር የማሳልፋቸው ግዜያት አይቆጩኝም ሲል ተደምጧል።

ሆኖም ይህ ግለሰብ በትላንትናው ዕለት በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ሀገሩ ያነሳችውን ዋንጫ እስር ቤት ወይስ ቤቱ ተመለከተ የሚለውን ብዙዎች ማወቅ ቢፈልጉም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን የገለጸው ነገር የለም ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-12-19