ከተጀመረ አንድ ዓመት የተጠጋው የእሁድ ገበያ በሁሉም ክ/ከተሞች እና እንዲሁም በተወሰኑ ክልሎች እየተካሔደ ይገኛል። አሁን ላይ በአዲስ አበባ ይህ ገበያ በቅዳሜ ቀንም እየተከናወነ ይገኛል።
በሀገሪቱ ያለው የኑሮ መወደድ እና የሸቀጦች ዋጋ መናር በተለይ በግብርናው ምርት ያለውን መወደድ ለማረጋጋት በሚል ዓላማ የተጀመረ ነው።
ነገር ግን እንደታሰበው የዋጋ ቅናሽ እያገኙበት እንዳልኾነ ለሳባቸውን ለጣቢያችን የገለጹ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር ተጠቃሚዎቹ በገበያው ሌሎች ተጨማሪ የግብርና ምርቶች በስፋት አለመቅረባቸው እንደ ክፍተት አንስተዋል። የገበያ ቦታዎቹም አመቺ ቦታ አለመኾናቸው በማንሳት መፍትሔ እንዲሰጠው ጠቁመዋል።
በዚሁ ገበያ በንግድ ላይ ተሰማርተው ያገኘናቸው ነጋዴዎች ግን የግብርና ምርቶቹ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከገበሬው የሚመጡ መኾኑን ገልጸው በቅናሽ ለተጠቃሚው እንደሚያደርሱ ነግረውናል። ወቅታዊ የኾኑ ምርቶች ላይ ግን የዋጋ ለውጥ ሊኖር እንደሚች ገልጸዋል።
የእሁድ ገበያ ተጠቃሚዎች ያነሱትን መፍትሔ የሚሹ ጥያቄዎችን ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አቅርበናል። የተነሱት ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ቡድን በማዋቀር ጥናት እየተደረገ እንደኾነ በቢሮ የንግድ ግብይት ማስፋፊያ ዳይሬክተር የኾኑት አቶ ደመቀ ሰይፈ ተናግረዋል።
ቀጣይ ፍብሪካዎች ምርቶቻቸውን በቀጥታ በእሁድ ገበያ መሸጥ የሚችሉበት መንገድ ይመቻቻል ተብሏል።በ97 አካባቢዎች ያለውን ገበያ ወደ 210 ለማሳደግ እቅድ ተይዟል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-12-20
