የዩክሬኑ መሪ ቮለድሚር ዘለንስኪ 300 ቀናትን በተሻገረው ጦርነት ዋነኛ አጋራቸውን ዋሽንግተንን ሊጎበኙ መሆኑ ተሰምቷል።
አሜሪካም ብትሆን የ1.8 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍን አዘጋጅታ እየጠበቀቻቸው ነው ተብሏል። በእሳቱ ላይ ነዳጅ የሚያርከፈክፈው እየበዛ 300 ቀናትን ተሻግሯል።
የኔቶ ወደ ምዕራቡ የመስፋት ጉዞ የጫረው እሳት በነ አሜሪካ አራጋቢነት እዚህ ደርሷል ባዮች በርካቶች ናቸው።
የአዛውንቱ የባይደን መንግስት አለሁልሽ ለሚሏት ኬቭ የ1.8 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተሰምቷል።
ከነጩ ቤት የመንግስት ሰዎች ሰማነው ሲሉ የምዕራባውያን ሚዲያዎች እንዳወሩት ከሆነ ዋሽንግተን እንደልጇ ከምታያቸው መሳሪያዎቿ መሀከል በራሷ እጅ የተመረተውን ዘ ፓትሪዮት የተሰኘውን የአየር መከላከያ እና ሚሳኤልን የጨመረ ነው።
ከዚህ በግዙፍ መኪና ጀርባ ላይ ከሚታዘል ሚሳኤል በተጨማሪ ከባድ ተተኳሾችንም ለዩክሬን ለመስጠት አቅደዋል ነው የተባለው።
የዩክሬኑም መሪ ቮለድሚር ዘለንስኪ የቁርጥ ቀን ወዳጃቸውን ጆ ባይደንን ለመገናኘት ወደ ዋሽንግተን ለማቅናት ጓዛቸውን ሸክፈው መነሳታቸው ተሰምቷል።
ይህ የዘለንስኪ የዋሽንግተን ጉዞ ጦርነቱ ከተጀመረ ለመጀመሪያ ግዜ የሚደረግ ነው።
ዘለንስኪም ቢሆኑ ከኬቭ ወጣ ካሉ ረዘም ያለ ግዜ ተቆትሯል።
መቼ በምን ሰዓት ጉዟቸውን ይጀምራሉ የሚለው፤ ለፕሬዚዳንቱ ደህንነት ሲባል እንደማይገለጽ ነው የተሰማው።
በርግጥ ይህ ጦርነት አሜሪካን ጨምሮ ለምዕራቡ ዓለም ኪሳራ አይደለም ይላሉ አንዳንዶች፤ በዚህ ጦርነት ብቻ ከትናንሽ የሀገራቱ የጦር መሳሪያ አቅራቢዎች እስከ ትላልቆቹ በቢሊየን የሚቆተሩ ዶላሮችን አጋብሰዋል።
ከዚህም ውስጥ አሜሪካ 299 ቢሊዮን ዶላር ገቢን በማግኘት የሚደርሳት የለም።
ወዲያ ደግሞ ኃይልን ከሩሲያ በመግዛት ይጠቀሙ ከነበሩት ሀገራት አንዷ የአውሮፓ ህብረቷ ሀገር ፈረንሳይ መሪ ኢማኗኤል ማክሮን አእረ የሰላም ያለህ እያሉ ነው።
ምዕራባውያን እና ኔቶ ለዩክሬን ሉዓላዊነት እና ድንበር መከበር መተመተማመኛ ለማግኘት ወገቡን እንዳጠበቀ ሁሉ ይህ መተማመኛ ለሩሲያም ሊረጋገጥላት ይገባል ያኔ ነው ሰላም ማምታት የምንችለው ሲሉ ተደምተዋል።
አስቀድሞም ቢሆን ማዕቀቦች እና እሩሲያን የህልውና ስጋት ውስጥ የሚከቱ እርምጃዎችን ከመውሰዳችን በፊት ተቀምጠን እንምከርበት ሲሉም እየተማፀኑ ይገኛሉ። በዚህ የማይስማሙ እና የማይተባበሩ ካሉ አህጉሪቱን ወደ ጦርነት እየማገዱ ነው ባይም ናቸው።
የክሮሺያው ፕሬዚዳንት ዞራን ሚልኮቪች በዚህ ሀሳብ የሚስማሙ ይመላሉ። በሀገራቸው የዩክሬን ወታደሮች እንዲሰለጥኑ የቀረበላቸውን ጥያቄ ወዲያ በሉልኝ ማለታቸው ተሰምቷል።
ሚልኮቪች ይህንን አሉ ዩክሬን አጋር ሀገር አይደለችም፤ በግድ የአውሮፓ ህብረት አካል እንድትሆን እየተደረገ ነው እንጂ። አሁንም ቢሆን ገና በእጩነት ነው ያለችው።
ይህ ተግባር ጦርነቱን በግድ ወደ ሀገሬ መጥራት ነው አላደርገውም አሉ። ይህ ሁሉ የተሰማው ሀገራቸው ክሮሺያ የአውሮፓ ህብረት ያዘጋጀውን 15 ሺሕ የዩክሬን ወታደሮች በክሮሺያ ይሰልጥኑ የሚል ፕሮግራም ላይ የሀገሪቱ ፓርላማ በድምፅ ብልጫ ውድቅ ካደረገው በኋላ ነው።
በየቀኑ አዲስ ነገር የማያጣው፤ በርካታ እንቆቅልሾች የከበቡት ጦርነት 301 ቀናትን አስቆጥሯል፤ 302 ሲል ምን ያሰማን ይሆን?
መልሱ የግዜ ነው።
በሳምሶን ገድሉ
2022-12-21
