የሴቶች እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ውሎ አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሕፃናት እና እናቶች ከሕፃን ልጆቻቸው ጋር መልሶ ማቋቋም የሚረዱ የተሀድሶ ማዕከላት የሚመደበው በጀት በአግባቡ እየተጠቀሙት ስለመኾናቸው አረጋግጦ እንዲያቀርብ ታዘዘ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከ 21 ሺ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት እንዲቋቋሙ አድርጊያለሁ ቢልም ዘለቄታዊ ሥራዎችን በመስራቱ ላይ ድክመት እንዳለበት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተናግሯል።
ውሎ አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ እናቶች በተሀድሶ ማዕከላት ከቆዩ በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት ፍላጎት ያላቸውን የነዋሪነት መታወቂያ እንዲያገኙ የማድረጉ ሒደት ላይ ክፍተት በመኖሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲያሻሻሽል ተጠይቆም ነበር።
በዚህ ጉዳይ ስለተሠራው ሥራ ሚንስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሁኔታዎች የነዋሪነት መታወቂያ መሠጠት ማቆሙ ሥራው ላይ ችግር እንደፈጠረ አንስተዋል። አሁን ላይ ግን የመታወቂያ አገልግሎቱ ከእንደገና በመጀመሩ ሥራው ይቀጥላል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባቀረው ሪፖርት አሁንም መሻሻል ያሉባቸው ጉዳዮች አሉ ኢሉ ተናግረዋል።
ከጎዳና የሚነሱ ዜጎችን በዘላቂነት ማቋቋም፣ ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት ሥራዎችን መሥራት ላይ ድክመቶች አሉ ብለዋል።
ከ 4 ዓመት በላይ የኾነው እና ለሚንስትሮች ም/ቤት እንዲጸድቅ የተላከው የማኀበራዊ ጥበቃ ፈንድ አዋጅ ሳይጸድቅ እስካሁን መቆየቱ እንደክፍተትም ተነስቷል።
እነዚህ የተነሱ የማሻሻያ ሀሳቦች እንዲስተካከሉ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-12-21
